
ባሕር ዳር: የካቲት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ ነጻ እና ተዓማኒ ምርጫ እንዲከናወን የወጣቶችን ሚና የተመለከተ ሥልጠና በአማራ ክልል በወጣቶች ክንፍ አሥተባባሪነት ሲሰጥ ቆይቷል። የማጠቃለያ መርሐ ግብርም ተከናውኗል።
በሥልጠናው የወጣቶች ፌዴሬሽን፣ የወጣቶች ማኅበር፣ የሁሉም ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች የወጣቶች ክንፍ አባላት ተሳታፊ ኾነዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ዓድዋ የአንድነት መገለጫ፣ የኢትዮጵያውያን ኩራት፣ የአፍሪካ ተምሳሌት በመኾኑ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
የሥልጠናው ተሣታፊዎች ሀገርን በመውደድ እና ለሕዝብ በመቆርቆር እንዲሠሩ አሳስበዋል። ከሥልጠናው ያገኛችሁትን ዕውቀት እና ልምድ በመውሰድ የበኩላችሁን ልትወጡ ይገባል ነው ያሉት።
በተለያየ ዘርፎች ውጤታማ በመኾን ስኬታማ መሪ ልትኾኑ ይገባል ብለዋል። መሪነት ራስን ከመግዛት ነው የሚጀምረው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ይህንን መነሻ በማድረግ ልትሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
ወጣቶች የምርጫ ካርድ እንዲያወጡ፣ ድምጽ እንዲሰጡ በማድረግ እና ራሳችሁም በመምረጥ ስኬታማ ምርጫ እንዲከናወን የበኩላችሁን ልትወጡ ይገባል ብለዋል።
በታዛቢነት በመሳተፍ ፍትሕዊ፣ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲከናወን ልትሠሩ ይገባል ነው ያሉት። ግጭት ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ሕጻናትን እና አረጋዊያንን ይጎዳል፤ ሁሌም ለሰላም ግንባታ ልትሠሩ ይገባል ብለዋል።
በቴክኖሎጂ ራስን በማብቃት፣ በኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና በመሳተፍ እና የሥራ ዕድል ተጠቃሚ በመኾን ሀገርን ከፍ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊዎች ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲከናወን የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ሃሰተኛ መረጃዎችን በመከላከል፣ ሰላምን በማጽናት ሀገርን በማስቀደም እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።
በመርሐ ግብሩ የአማራ ወጣቶች ማኅበር መመዝገብ እና መረጃ ማግኘት የሚችሉበት ድህረ ገጽ ተመርቋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
