ትውልዱ የዓድዋን ድል ለመድገም አንድነትን ማጠናከር አለበት።

1
ባሕር ዳር: የካቲት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓድዋ ኢትዮጵያውያን በመተባበር ሉዓላዊነታቸውን እና ነጻነታቸውን ያስከበሩበት ነው።
ለዓለም ጥቁር ሕዝቦችም ድል ነው። በአፍሪካ ለነጻነት ለሚታገሉ እና በዓለም ላይም በዘረኝነት ተጽዕኖ ሥር ለነበሩ ሕዝቦች የመነሳሳት እና የኩራት ምንጭ ነው።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አሥተዳደር ትምህርት ክፍል የታሪክ መምህር ገረመው እስከዚያ (ዶ.ር) ስለ ዓድዋ ድል እና አስተምህሮው ለአሚኮ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ከበርካታ ክብርና ታሪኮቿ መካከል አንዱ እና ዋናው የዓድዋ ድል መኾኑን ዶክተር ገረመው ገልጸዋል። የአፍሪካ መዲናነት ምንጩም ይኼው የዓድዋ ድል መኾኑን ጠቅሰዋል።
ዓድዋ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በዓለም ትልቅ ቦታ እንዲኖራት፣ ኢትዮጵያውያን በነጭ የዘረኝነት አስተሳሰብ እንዲላቀቁ እና በኩራት እንዲኖሩ አድርጓል።
አጼ ምኒልክ በአዋጃቸው ”ለሀገርህ፣ ለክብርህ፣ ለነጻነትህ…ስትል ተከተለኝ” ብለው ባወጁ ማግሥት ኢትዮጵያውያን ከሁሉም አቅጣጫ ነው ሆ! ብለው የዘመቱት።
ቅኝ ለመግዛት የመጣን ወራሪ ድል መትተው የመለሱት በትብብር መኾኑንም አመላክተዋል። እነ ጆርጅ በርክለይም የአጼ ምኒልክን እና የእቴጌ ጣይቱን የአመራር ብስለት እና ጀግንነት የሕዝቡን ለሀገሩ ቀናኢነት ዘግበው ለዓለም አሰራጭተዋል።
በዓድዋ ዘመናዊውን የአውሮፓ ኀይል እንዴት ጥቁር ሕዝብ አሸነፈው በሚልም ለዓለም መደነቂያ መኾኑን ነው ዶክተር ገረመው ያስታወሱት።
በዓድዋ ዘመቻ ያልተሳተፈ እንደሌለና ሴቶች፣ ቀሳውስት እና አካል ጉዳተኞች ሳይቀር እንደነበሩ በርክለይ መጻፉን የታሪክ ምሁሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ቅንነት እና አንድነት ብቻ ሳይኾን ጦር አዋቂ ጀግኖች መኾናቸውንም ዶክተር ገረመው ገልጸዋል።
የካቲት 23/1888 ዓ.ም በጣሊያን ጦር አዛዥ ጄኔራል ባራቲየሪ መሪነት ጦርነቱ ሲጀመር ጄኔራል አልቤርቶኒን እነ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ማረኩት። ጄኔራል ዳቦር ሜዳ እና አርሞንዲም ተገደሉ። በርካቶችም ለሞት እና ምርኮ ተዳረጉ ብለዋል የታሪክ ምሁሩ።
በዲፕሎማሲ ረጅም ጊዜ ትግል ቢደረግበትም ጦርነቱ ግን በአንድ ቀን የተጠናቀቀ ነው። የዓድዋ ድል ከአንድነት የመነጨ ጭምር መኾኑን ጠቅሰው በዚህ ዘመንም ለሁሉም ትግል አንድነት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ቅኝ የተገዙ ሀገራት በቅኝ ግዛት ዘመን ምን ያህል ነጻነታቸውን አጥተው በሁለተኛ ዜጋነት እንደኖሩ ታሪክ ጠቅሰው ተናግረዋል።
ቅኝ ገዢዎች ጥሬ ሀብትን ለመዝረፍ እንዲመቻቸው መሠረተ ልማቶችን መዘርጋታቸውን ጠቅሰው ነጻነት ግን ከዚያ ሁሉ በላይ መኾኑን ነው የገለጹት።
ምሁሩ ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስጠብቃ በመኖሯ በአፍሪካ ያላትን ተሰሚነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት አንስተዋል። የአፍሪካዊነት (Pan – Africanism) ንቅናቄ መነሻ መኾኑንም አንስተዋል።
ቀደምት አባቶች ያለ ዘመናዊነት በቅንነት እና በትብብር ኢትዮጵያን አስከብረው ቆይተዋል። የአሁኑ ትውልድም ሀገር ወዳድነትን እና አንድነትን መማር እንደሚገባው አንስተዋል።
ወጣቶች ሀገር የሚያድገው በልማት መኾኑን ተገንዝበው ለልማት መትጋት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል። የኢኮኖሚ ልማት እንዲመጣ ሁሉም በየተሰለፈበት ሙያ መትጋት እንዳለበት አንስተዋል።
በኅዳሴው ግድብ የታየውን መነሳሳት እና ተሳትፎ የጠቀሱት ዶክተር ገረመው ውጤቱም የምጣኔ ሃብት ሉዓላዊነት እንደሚያስገኝ ገልጸዋል። በቀጣናውም ለሚኖር ትስስር አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
ድህነትን በማሸነፍ ሌሎች ችግሮችንም ማሸነፍ ይቻላል። ቴክኖሎጂን መጠቀም ጊዜው የሚጠይቀው ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ማስከበሪያ ነውም ብለዋል።
በሁሉም ዘርፍ ንቁ ተሳታፊ በመኾን፣ ከከፋፋይ ሃሳቦች ይልቅ ለአንድነት በመትጋት፣ የዓድዋን ገድል እና ራዕይ ማሳካት እንደሚያስችል ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየዓድዋ ድል ሚስጢሩ የኢትዮጵያውያን የዓላማ ጽናት እና የሀገር ፍቅር ነው።
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ።