ዓድዋ የኢትዮጵያ አንድነት የተጠናከረበት ታሪካዊ መሠረት ነው።

1
ባሕር ዳር፡ የካቲት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በፓውሎስ ኞኞ “አጼ ምኒሊክ” መጽሐፍ ላይ እንደተፃፈው
የዓድዋ ጦርነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያለው ክስተት ነው።
ነገር ግን ዓድዋ በተለምዶ እንደሚታወቀው የጦር ድል ብቻ አይደለም፤ ሀገራዊ አንድነት የተፈተነበት እና የተጠናከረበት ታሪካዊ ነጥብ እንጅ ።
መጽሐፉ ዓድዋን እንደ ታሪክ ክስተት ብቻ ሳይኾን፣ እንደ ብሔራዊ አንድነት ብሎም ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መሠረት መኾኑን ያትታል።
በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በአፍሪካ ላይ የቅኝ ግዛት ተወዳዳሪነት ከፍ ያለበት ዘመን ነበር። ኢትዮጵያም በዚህ የውጭ ጫና መካከል ነበረች። እንደ መጽሐፉ ትንታኔ፣ የዓድዋ ጦርነት የተካሄደው ከእነዚህ የቅኝ ግዛት ሙከራዎች ጋር በተያያዘ ነበር።
በአጼ ምኒሊክ መሪነት ሕዝብ ከልዩ ልዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአንድነት ተነሳ። ይህ የተደራጀ ኀይል በዓድዋ ድል የተገለጠ ብሔራዊ አንድነት ነበር።
ደራሲው ዓድዋን የተደራጀ የሕዝብ ኃይል እና የመንፈሳዊ ጽናት ምሳሌ እንደኾነ ያቀርበዋል።
ድሉ በመሣሪያ ኃይል ብቻ አልተገኘም፣ በአንድነት እምነት እና በሀገር ፍቅር ታግዞ እንጅ።
ከድሉ በኋላ ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ዕውቅና ያገኘች ሀገር ኾነች። ዓድዋ የመንግሥት መዋቅርን ለማጠናከር የረዳ ታሪካዊ መሠረትም ነበር።
የውጭ ግንኙነት ላይ እምነት ጨመረ፤ የመንግሥታዊ አንድነት አቅም ተጠናከረ፤ የብሔራዊነት ሥነ ልቦና ዕድገትም ከፍ አለ።
እነዚህ ሁሉ ዓድዋን ከጦር ድል በላይ ወደ ሀገር ግንባታ እና አንድነት መሠረት እንዲለወጥ አድርገውታል።
መጽሐፉ ዓድዋን እንደ ታሪካዊ ክስተት ብቻ አይመለከትም፤ እንደ ብሔራዊ ምልክት ይቆጥረዋል። ለትውልድ የሚተላለፍ የነፃነት ተምሳሌት እና የአንድነት መንፈስም ነው ዓድዋ።
ይህም በየዓመቱ እንደ መታሰቢያ ቀን እንዲከበር ብቻ ሳይኾን፣ እንደ ብሔራዊ ራዕይ እንዲታይ አድርጎታል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአዘርባጃን የተለያዩ ተቋማትን ጎበኙ።
Next article‎ከዓድዋ ድል ወጣቶች ምን ይማራሉ?