የመንግሥት አሥተዳደር ሪፎርም የመንግሥት ተቋማት ግልጽ አሠራር እንዲኖራቸው ያደረገ ነው።

5
ባሕር ዳር: የካቲት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ፈጣን እና ጥራት ያለው አገልግሎትን ለማረጋገጥ በ2018 በጀት ዓመት የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን ተግባራዊ አድርጓል። ቢሮው በግማሽ ዓመቱ የዕቅድ አፈጻጸም ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የተገኙት የምዕራብ ጎጃም ዞን ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ የሻረግ ታፈረ የመንግሥት አሥተዳደር ሪፎርም የመንግሥት ተቋማት ግልጽ አሠራር እንዲኖራቸው ያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
ተቋማት በተቀመጠው ስታንዳርድ አገልግሎት እንዲሰጡ፣ ተገልጋዮችም በፈጠነ መንገድ አገልግሎት እንዲያገኙ እድል የፈጠረ ነው ብለዋል።
በቡሬ እና ፍኖተ ሰላም ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለማቋቋም ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ተገልጋዮች ባሉባቸው ተቋማት በሪፎርም አተገባበሩ ላይ በተሠራ የዳሰሳ ጥናት የደንበኞችን ርካታ ከነበረው 60 በመቶ ወደ 81 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ የሪፎርም ድጋፍ እና ክትትል ቡድን መሪ ወርቁ ይሁኔ አገልግሎት አሠጣጡን ለማሻሻል ከተዘረጉ አሠራሮች ውስጥ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት አንዱ ነው ብለዋል። በከተማ አሥተዳደሩ ዜጎች የተቀናጀ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ ሥራ እየተካሄደ መኾኑን አንስተዋል።
አስር የመንግሥት ተቋማትን እና 104 አገልግሎቶችን ወደ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለማስገባት ተለይተዋል። ከግንባታው ጎን ለግን ቴክኖሎጅ ሲስተም የማልማት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ነው የገለጹት።
ማዕከሉ ተጠናቅቆ ወደ ተግባር ሲገባ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን እንግልት ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል። ሪፎርሙ የተቋማትን የመፈጸም አቅም ያሻሻለ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleሙስና መረጃው ድብቅ፣ የምርመራ ሥራውም ረቂቅ ነው።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአዘርባጃን የተለያዩ ተቋማትን ጎበኙ።