
ባሕርዳር፡ የካቲት 20/2018 (አሚኮ) የአማራ ክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሙስና አና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ከክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እና ፍትሕ ቢሮ ጋር በቅንጅት በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ ውይይት አድርጓል።
የአማራ ክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ እንደ ኮሚሽን ሙስናና ብልሹ አሠራርን በመከላከል ትውልድ ለመገንባት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የሙስና ብልሹ አሠራር እንደሀገር እና እንደ ክልል እንደ አንድ የተለየ ችግር መኾኑን ተናግረዋል። ችግሩን ለመፍታት ደግሞ መንግሥት አሳሳቢነቱን ተረድቶ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ነው የጠቀሱት።
በማሳያነትም ብልሹ አሠራርን ለመከላከል የተቋማትን አሠራር ዲጅታላይዝድ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። በየአካባቢው ተቋማት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉንም አንስተዋል።
ኮሚሽኑ ደግሞ ከብዙ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት። ከፖሊስ እና ፍትሕ አካላት ጋር የሀብት ምዝገባ እና ማጣራት፣ የአሠራር ጥናት እና አስቸኳይ ሙስና መከላከል፣ ጥቆማዎች ሲመጡም ለሚመለከተው አካል በመላክ በኩል ተቀናጅተው እየሠሩ እንደኾነ ተናግረዋል።
ሦሥቱ ተቋማት ተቀናጅተው በመሥራታቸው ከጅምር ባለፈ አመርቂ ውጤት መጥቷል ተብሎ እንደማይታሰብም ጠቅሰዋል። በጅምር ደረጃ በተሠሩ ሥራዎች ወንጀለኞች ተጠያቂ እንዲኾኑ የማድረግ፣ ተቋማት ለብልሹ አሠራር እና ሙስና የተጋለጡ አሠራራቸውን እንዲያስተካክሉ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
ሙስና እና ብልሹ አሠራርን በዋናነት ለመከላከል ተቋማት መረጃዎችን የመለዋወጥ፣ በጋራ ማስረጃዎችን የማሰባሰብ፣ በጋራ ወንጀለኞችን ተጠያቂ የሚያደርጉ ሥራዎችን መሥራት በቀጣይ ትኩረት እንደሚሰጥባቸው ገልጸዋል። በየተቋማቱ የሚታዩ አሠራሮችን በጋራ የማጥራት ሥራዎችም ትኩረት እንደሚደረግባቸው አንስተዋል።
የመንግሥት ሀብት ከመመዝበሩ በፊት መከላከል፣ ተመዝብሮ ሲገኝ ደግሞ ተገቢ ክትትል አድርጎ የማስመለስ ሥራ በቅንጅት እንደሚሠራም ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ቀደም ሲል ከሙስና እና ብልሹ አሠራር ጋር ተያይዞ ቅንጅታዊ አሠራሮች ተግባራዊ ሲደረጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በዛሬው ውይይትም ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር የሀብት ምዝገባ እና ማጣራት፣ ቅንጅታዊ አሠራር እና ከጥቆማ አሠጣጥ ጋር ተያይዞ ሲያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን ለማረም መኾኑን ነው የጠቀሱት። እንደ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያው ከዚህ በፊት ከመሬት ወረራ እና ከግዥ ሥርዓት ጋር ተያይዞ ይበልጥ በትኩረት ሲሠራ መቆየቱን አንስተዋል። በሚፈለገው ልክ ግን ውጤት መጥቷል ማለት እንደማይቻል ነው የጠቀሱት።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ክልሉ በጸጥታ ችግር መቆየቱ ብልሹ አሠራር እና ሙስናን በተገቢ ኹኔታ የመከላከል ተግባር ላይ ውስንነቶች እንዲኖሩ ያደርጋል ነው ያሉት።
በውይይቱ ሲሳተፋ ያገኘናቸው የሰሜን ጎጃም ዞን ፍትሕ መምሪያ የዞን አቃቢ ሕግ እና የሙስና ወንጀል የሥራ ሂደት አስተባባሪ ኀይሌ ጥሩነህ የሙስና እና ብልሹ አሠራር ወንጀል መረጃው ድብቅ እና የምርመራ ሥራው ረቂቅ መኾኑን ተናግረዋል።
የሙስና ወንጀል በባሕሪው ከመደበኛ ወንጀል እንደሚለይም አንስተዋል። ለዚህ ደግሞ ተቀናጅቶ መሥራት እና ውጤት ማምጣት ያስፈልጋል፤ በቀጣይም ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ ተቀናጅተን እንሠራለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
