
ከሚሴ፡ የካቲት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመወዳደሪያ ማኒፌስቶውን እና የምርጫ ምልክቱን አስተዋውቋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሕመድ ሁሴን ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ለትውልድ የሚሸጋገሩ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ተናግረዋል።
የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፓርቲው መሪዎች እና አባላት እንደሚሠሩም ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም በመራጮች ምዝገባ በንቃት እንዲሳተፍም አሳስበዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደቻለም ተናግረዋል።
የፓርቲው ፍኖተ ካርታ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሻገር መኾኑንም ጠቅሰዋል። የምርጫ ምልክቱም ”የስንዴ ነዶ” መኾኑን ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል።
ዘጋቢ :- ይማም ኢብራሒም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
