
ባሕር ዳር: የካቲት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የ2018 ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና በአዲሱ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ላይ ውይይት እያካሄደ ነው።
የቢሮው ኀላፊ ባንቻምላክ ገብረማርያም እንዳሉት በ2018 ዓ.ም ስድስት ወራት የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርምን ለመተግበር ሕግ ከማውጣት ጀምሮ አሠራሮችን እና ስትራቴጅዎችን የማዘጋጀት ሥራ ተሠርቶ በተመረጡ ተቋማት ተግባራዊ ተደርጓል። ሪፎርሙ በተተገበረባቸው ተቋማትም የአገልግሎት አሠጣጡን ያዘመነ መኾኑን አንስተዋል።
የክልሉን ሕዝብ መልካም አሥተዳደር ችግሮች ለመፍታት ተቋማት ዲጅታላይዝ እንዲኾኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም አካል የኾነው ሞሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በደሴ እና ባሕር ዳር ከተሞች አገልግሎት እንዲጀምር ተደርጓል። በጎንደር ከተማም በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛል ተብሏል።
ከዚህም ባለፈ በክልሉ በሚገኙ አምስት ሪጅኦፖሊታን ከተሞች እና በሌሎች 25 አነስተኛ ከተሞች በቅድመ ዝግጅት ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ሪፎርሙ በተሟላ መንገድ እንዲተገበር የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉም ቢሮ ኀላፊዋ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
