ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን በአግባቡ መጠቀም አለባቸው።

4
ደብረብርሃን፡ የካቲት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎የመምረጥ እና የመመረጥ መብት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 38 መሠረት ለዜጎች ዕውቅና የተሰጠ ዴሞክራሲያዊ መብት ነው።
ይህንን መብት ዜጎች በአግባቡ እንዲጠቀሙት ለማድረግም የማስፈጸሚያ አዋጆች እና ደንቦች በየጊዜው ወጥተዋል።
‎ምርጫ ዜጎች በእኩልነት፣ በነጻነት፣ በገለልተኛነት፣ ተአማኒ በኾነ መንገድ በምስጢር በሚሰጡት ድምጽ መሪዎቻቸውን የሚመርጡበት ነው። የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ መኾኑን ማሳያ ነው።
‎ይህም የዛሬውንም ይሁን የነገውን ትውልድ ዕጣ ፈንታ የመወሰን ጉዞ መኾኑን ጠበቃ እና የሕግ አማካሪው ዳንኤል ጥላሁን አብራርተዋል።
በምርጫው ቀን ዜጎች ለዛሬም ይሁን ለነገው ትውልድ ይበጃል ያሉትን መምረጥ አለባቸው ያሉት አቶ ዳንኤል ለዚህም ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
‎በምርጫ ሕጉ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ያልተመዘገበ ሰው መምረጥ ስለማይችል ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ቀዳሚው ተግባር የመራጮች የምዝገባ ወቅት ሳያልፍ መመዝገብ እና የመራጭነት ካርድ መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
‎ከዚያ ባለፈም የምረጡኝ ቅስቀሳ በሚደረግበት ጊዜ በንቃት መከታተል፣ የፓርቲዎችን ዕቅድ ማወቅ እና ማንን መምረጥ እንዳለባቸውም መረዳት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
‎በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38 ላይ እንደተቀመጠው የምርጫ መርሆዎች በምርጫ ሕጉ አንቀጽ አምስት ላይ መቀመጣቸው፣ መንግሥት የሚመሠረተው ነጻ በኾነ ምርጫ መኾኑ በሕገ መንግሥቱም ይሁን በምርጫ ሕጉ መቀመጡ እና የምርጫ ሥነ ሥርዓቱ በግልጽ የተደነገገ መኾኑ ምርጫውን ለማሳለጥ የተጣጣመ የሕግ አሠራር መኖሩን አንስተዋል።
‎በዚህ ወቅት የፓርቲዎች እንቅስቃሴ የምርጫ ሥነምግባርን ባከበረ መልኩ መኾን እንዳለበት በምርጫ ሕጉ አንቀጽ 127 ጀምሮ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን በማንሳት አብራርተዋል።
በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ያለው ምርጫ እንዲካሄድ ፓርቲዎች ለሕዝባቸው ግልጽ የኾነ ፖሊሲ ማቅረብ፣ ከጥላቻ ንግግር መቆጠብ፣ እርስ በእርሳቸው መከባበር እና ሰላማዊ የኾነ የምርጫ ሂደትን መከተል ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
‎በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 መሠረት ገለልተኛ ኾኖ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ውጤታማ እንዲኾን እየሠራ እንደሚገኝ ተረድተናል ብለዋል።
ለዚህም ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብ እንዲፈርሙ መደረጋቸው፣ የእጩዎች ምዝገባ በቴክኖሎጂ መታገዙ፣ የጊዜ ሰሌዳ መውጣቱ፣ የቅሬታ መፍቻ መንገድ መቀመጡ እና መሰል ተግባራት ለምርጫው በቂ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን እንደማሳያ ጠቅሰዋል።
‎ምርጫው ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ሰላማዊ የኾነ እና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው እንዲኾን ገለልተኛነቱን ማስጠበቅ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚጠበቅ ተግባር መኾኑን አስረድተዋል።
ምርጫውን ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታ በሌለባቸው ቦታዎች ላይ መንግሥት ጠንከር ያለ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦‎ደጀኔ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በባኩ የክብር ዓደባባይ የአበባ ጉንጉን አስቀመጡ።
Next articleተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ በቁጭት መሥራት ያስፈልጋል።