
ባሕር ዳር: የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በ1971 ዓ.ም በዩኔስኮ ሲመዘገብ 136 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ነበረው። ፓርኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማስፋፊያ እየተደረገለት አሁን ላይ ወደ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር እንዲሰፋ ተደርጓል። የፓርኩ የዓለም ቅርስነት ማፅደቂያ አዲስ ሰነድ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሂዷል።
የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኀላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከክልሉ እና ከሀገር አልፎ የዓለም ሀብት ነው ብለዋል። ይህንን ሀብት ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ የብዝኀ ሕይወት ጥበቃ እና ሌሎች በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል ነው ያሉት።
ከኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እና ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር ፓርኩ በዩኔስኮ እንደ አዲስ እንዲመዘገብ የማስፋት እና ተገቢ ጥበቃ እየተደረገለት ነው ብለዋል።
ሕገ ወጥ እርሻ፣ ሕገ ወጥ አደን፣ የሰደድ እሳት እና መሰል ለፓርኩ አደጋ የኾኑ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን በመከላከል ፓርኩ የዓለም ቅርስ ኾኖ እንዲቀጥል የተጠናከረ ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ በፊት በዩኔስኮ የተመዘገበው አነስተኛ ክፍል ነበር ያሉት ኀላፊው በተቀናጀ ሥራ የፓርኩ ክፍል ሰፍቶ እና ተጠናክሮ እንደ አዲስ ለማስመዝገብ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በሀገር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ በአራት ጉዳዮች ልዩ መኾኑን ገልጸዋል።
በሌላው ዓለም የማይገኘው ዋልያ አይቤክስ መገኛ መኾኑ እና ድንቅ መልክዓ ምድር ያለው መኾኑ በዓለም ልዩ ያደርገዋል ብለዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ የሀገሪቱ ትልቁ ተራራ መገኛ እና በዩኔስኮ ከተመዘገቡት ውስጥ ግንባር ቀደም በመኾኑ ልዩ መኾኑን አንስተዋል።
ብሔራዊ ፓርኩ በዓለም ቅርስነት ሲመዘገብ ፓርኩ እንዲመዘገብ ያስቻሉ ብርቅዬ እንስሳት ከፓርኩ ውጭም ይገኙ ስለነበረ ፓርኩን በማስፋት እንስሳት የሚገኙበትን በፓርኩ ውስጥ በማካለል በአዲስ መልክ የፌደራል መንግሥት እያሥተዳደረው እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በፓርኩ ላይ የተደረገውን ማስፋፊያ እንደገና ማስመዝገብን ዩኔስኮ ያስገድዳል ያሉት ዳይሬክተሩ ዩኔስኮ የሚፈልጋቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አሟልቶ ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
ከሥነ ውበት፣ ከገጽታ፣ በውስጡ ከሚገኙ ብርቅዬ እንስሳትን እና ብዝኀ ሕይወት ጋር በተያያዘ ሳይንሳዊ ትንተና ተካሂዶ ዩኒስኮ ሊቀበለው የሚችል ሰነድ ተዘጋጅቶ መላኩንም ጠቅሰዋል። ሰነዱ ፓርኩን መልሶ ማስመዝገብ እንደሚችል ታምኖበታል ነው ያሉት።
ፓርኩን አስፋፍቶ በአዲስ መልክ በዩኔስኮ ማስመዝገብ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል። ፓርኩ የዓለም ሀብት በመኾኑ ዓለም አቀፍ ትኩረት እና ድጋፍ እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል።
የቱሪዝም እድገቱን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል፤ በዚህም ለሀገር ገጽታ ግንባታ እና ለማኅበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ ይኾናል ነው የተባለው። ለፓርኩ ብዝኀ ሕይወት ጥበቃ መጠናከርም ትልቅ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
