የኮሪደር ልማት ከውበት ባሻገር

10
ባሕር ዳር፡ የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኮሪደር ልማት ከተሞችን ለመኖር ምቹ ማድረግ፣ ማደስ፤ ገጽታን ማሻሻል እና ከልማቱ ሁሉም ተጠቃሚ እንዲኾን የማስቻል ዓላማ ያለው ተግባር ነው።
በኢትዮጵያ የኮሪደር ልማት ተግባራዊ እየተደረገባቸው ከሚገኙ ከተሞች መካከል ደግሞ ባሕር ዳር አንዷ ናት። ከተማዋ በሁለት ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ተግባራትን ስታከናውን ቆይታ አሁን ላይ ወደ ሦስተኛ ምዕራፍ ተሸጋግራለች።
በዚህ የከተማ ልማት ሂደት ተሳትፎ ካላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ሃጅ ተዘራ አበበ ይጠቀሳሉ።
ሃጅ ተዘራ በባሕር ዳር ከተማ 50 ዓመታትን ኖረዋል። ለባሕር ዳር ከተማ ልዩ ፍቅር አላቸው። ፍቅራቸውን ሲገልጹ እንደ ኒወርክ ከተማ ብትኾን ሲሉም ምኞታቸውን ተናግረዋል።
ብዙ ዓመት ከተማዋ ላይ እንደኖረ ነዋሪ የከተማዋ የልማት እቅስቃሴ እና እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ መምጣቱንም ትዝብታቸውን አጋርተዋል።
ከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን መሥራት ከጀመረች ጊዜ አንስቶ ባሕር ዳር ካላት ውበት በላይ የበለጠ ደምቃለች ነው ያሉት። በዚህም እርሳቸው እና በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ኮሚቴ በማዋቀር ተሳትፎ እያደረጉ እንደኾነም ተናግረዋል። የኮሪደር ልማት ሥራዎች ተሳትፏቸውን እንደሚቀጥሉም ጠቅሰዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥራ አሥኪያጅ ተሻገር አዳሙ የኮሪደር ልማት በባሕር ዳር በ2017 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰዋል። ጣናን የገለጠው 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ተጠናቅቆ ለሕዝብ ክፍት መኾኑንም አንስተዋል።
6 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ካለው ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራም 3 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የሚኾነው ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ገልጸዋል። ቀሪውም የአፈጻጸም እና ተያያዥ ሥራዎቹ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ይሰጣሉ ብለዋል።
አሁን ላይ ሦስተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል። በዚህ ዙር በቆየ መጠሪያው ከጊዮን ሆቴል ጀምሮ እስከ ዘጌ መገንጠያ ያለው የ4 ነጥብ 3 እና ከአጂፕ እስከ ዓባይ ማዶ ገብርኤል ያለው የ3 ነጥብ 7 በድምሩ የ8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ በጥራት እና ቅልጥፍና እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ከጊዮን ሆቴል እስከ ገጠር መንገድ ድረስ ያለው ሥራ በጥንቃቄ ሂደት ላይ መኾኑን አንስተዋል። ይህንም በአንድ ወር ውስጥ አጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ኮሪደር ልማት ሢሠራ ከዲዛይን ጀምሮ የተቀናጀ የተቋማት ተሳትፎ ያለበት እንደኾነም ጠቅሰዋል። በአብነትም የቴሌ፣ የመብራት እና ውኃ መስመሮች ዝርጋታ ሥራዎችን አንስተዋል። ለቀጣይ 40 እና 50 ዓመታት ታሳቢ ተደረጎ እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
የኮሪደር ልማቱ ወጥ የኾነ የአረንጓዴ ልማት፣ የብስክሌት እና እግረኛ መንገድ ያለው ኾኖ ደረጃውን ጠብቆ እየተሠራ እንደኾነም ጠቅሰዋል።
በፍጥነት የሚደርሱ ምግቦች መሸጫዎች፣ የብስክሌት ማቆሚያ ቦታዎች፣ የታክሲ እና አውቶብስ ማቆሚያ ፌርማታዎች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሱቆች፣ ካፌዎች፣ መዝናኛ ቦታዎች፣ መናፈሻዎች፣ የሕጻናት መጫወቻ ቦታዎች እና ሞሎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች የተካተቱበት እንደኾነም ገልጸዋል።
ሕዝቡ የኮሪደር ልማቱን እየደገፈ እና እየተሳተፈ ነው ብለዋል። የከተማዋ ማኅበረሰብ ትብብር እና ተሳትፎ ሊደነቅ እና ሊመሠገን የሚገባው እንደኾነም አንስተዋል።
በኮሪደር ልማቱ በ2017 ዓ.ም ለ19 ሺህ፣ በ2018 ዓ.ም ደግሞ ለ20 ሺህ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል። የኮሪደር ልማት የሥራ ባሕል የዳበረበት መኾኑንም አንስተዋል።
የባሕር ዳር ኮሪደር ልማት ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ከተማዋ ካላት ውበት በላይ ውበት እና ድምቀት በመፍጠር የበለጠ የቱሪዝም መዳረሻ እንደሚያደርጋትም ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article
Next articleአቢሲኒያ ባንክ በ”ይጀምሩ ያድሱ ይደጉ” መርሐግብሩ አዳዲስ ደንበኞች ማፍራቱን ገለጸ።