3

“ብልጽግና ፓርቲ እፈጽማለሁ ያላቸውን ጉዳዮች በተግባር ማሳካት ችሏል” አቶ አወቀ አስፈሬ

ጎንደር፡ የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፓርቲውን ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት የማስተዋወቂያ መርሐ ግብር አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋሲል ሰንደቁ ፓርቲው በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የገባቸውን ቃሎች በተግባር ፈጽሞ ያሳየ እንደነበር አንስተዋል።

ፓርቲው ለሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዝግጅት አድርጓልም ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ትላንትን በመዘከር፣ ዛሬን በመትጋት ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማሸጋገር ሂደት ላይ መኾኑንም አቶ ፋሲል አመላክተዋል።

ፓርቲው በዴሞክራሲ ግንባታ ለአፍሪካ ተምሳሌት የምትኾን ሀገርን የመገንባት ራዕይን ይዞ የተነሳ መኾኑንም አብራርተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ምልክት “የስንዴ ነዶ” ነው፤ ስንዴ የአንድነት፣ የትብብርና የአቃፊነት ምልክት ነው ብለዋል አቶ ፋሲል።

የብልጽግና ፓርቲ አባላት እንደ “ስንዴ ነዶ” በአንድነት በመቆም እና በመተባበር ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት አሻራችሁን ማሳረፍ አለባችሁ ሲሉም አስገንዝበዋል።

መጭው 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ብልጽግና ፓርቲ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ ብልጽግና ፓርቲ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና ማኅበራዊ ዘርፍ እፈጽማለሁ ያላቸውን ጉዳዮች በተግባር ማሳካት መቻሉን አንስተዋል።

ፓርቲው በቀጣይ የኢትዮጵያን እድገት ከፍ ለማድረግ በትኩረት ይሠራልም ብለዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት የነበረውን የፕሮጀክት አፈጻጸም በማስቀጠል የኢትዮጵያን እድገት ያበስራልም ነው ያሉት።

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ እና ተአማኒ እንዲኾንና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ በጋራ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ ደስታ ካሳ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምርጫ ለሁሉም እኩል ሜዳ የሚፈጥር ሂደት ነው።
Next articleየኮሪደር ልማት ከውበት ባሻገር