
ጎንደር: የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በብልጽግና ፓርቲ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት የማስተዋወቂያ መርሐ ግብርን አካሂዷል።
ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ ሃብት ተጠቅማ ወደ ፊት መራመድ እንደሚገባት ያነሱት በብልጽግና ፓርቲ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ መኮንን ናቸው። ፓርቲው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመገንባት ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማስፈን የወል ትርክት ለመገንባት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ አካታችነትን እና ብዝሃነትን ይተገብራል ያሉት ኀላፊው በሕግ እና በአሠራር ላይ የተመሠረቱ እና ሀገርን የሚያስቀጥሉ ተቋማትን ለመገንባት እንደሚሠራ ነው የገለጹት። ፓርቲው መልካም አሥተዳደር፣ ሰላም እና ፍትሕ እንዲሰፍን ይሠራልም ብለዋል።
ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ የፓርቲው ግብ መኾኑንም አቶ ተስፋ አንስተዋል።
ምርጫ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መኾኑን ያነሱት ደግሞ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ናቸው። ብልጽግና ፓርቲ የማይቻሉ የሚመስሉ የልማት ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ሠርቶ በማሳየት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ዜጎች የመሠከሩለትን ተግባር መሥራት የቻለ ፓርቲ መኾኑን ገልጸዋል። የሕዳሴ ግድብን መጠናቀቅ በማሳያነትም አንስተዋል።
“ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊ እና ለሁሉም ዕኩል የኾነ ሜዳ የሚፈጥር እንደኾነም ነው” የገለጹት።
ዘጋቢ፦ ማርታ አዱኛ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
