
ደሴ፡ የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ማኒፌስቶ እና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት የማስተዋወቂያ መርሐ ግብር አካሂዷል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉጌታ አቢ ፓርቲው ባለፉት ዓመታት የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።
“በመደመር እሳቤ ለሀገራዊ አንድነት ብዙ ተጉዘናል” ያሉት ኀላፊው ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል የተሠሩት ሥራዎች የሚያኮሩ መኾናቸውን አመላክተዋል።
በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፓርቲው የምርጫ ምልክቱን የስንዴ ነዶ ማድረጉን ገልጸዋል። በቀጣይ የፓርቲውን ሕልም እና እቅዶች በማሳካት ረገድ በጋራ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
በከተማዋ ምርጫው ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ምቹ መደላድል እየተፈጠረ መኾኑንም ገልጸዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሙሀመድአሚን የሱፍ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሚጣልበት እና የሕዝብ ሉዓላዊነት በተግባር የሚረጋገጥበት ይኾናል ብለዋል።
ምርጫው ፍትሐዊ፣ ተዓማኒነት እና ቅቡልነት ያለው ምርጫ እንዲኾን መሥራት እንደሚገባም አብራርተዋል።
ምርጫው ሰላማዊ ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ በኾነ መንገድ እንዲከናወን ብልጽግና ፓርቲ ቁርጠኛ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን አሰፋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
