
ባሕር ዳር፡ የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የጤና አገልግሎት በሚሰጥባቸው የመንግሥት ተቋማት ላይ ታካሚዎች የሚታዘዝላቸውን መድኃኒት ከመንግሥት ተቋማት ስለማያገኙ ከግል መድኃኒት መደብሮች በከፍተኛ ዋጋ ለመግዛት ሲገደዱ ይስተዋላል።
ለመኾኑ በመንግሥት የጤና ተቋማት ያለው የመድኃኒት አቅርቦት ምን ያክል ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ይኾን?
ወይዘሮ አበበች አየልኝ ልጃቸውን ለማሳከም ከቋራ ወደ ባሕር ዳር ፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል መምጣታቸውን ነግረውናል፡፡ የጤና መድኀን አገልግሎት ተጠቃሚ ሲኾኑ በሆስፒታሉ በነጻ ሕክምና አገልግሎት እንዳገኙም ገልጸዋል፡፡
የታዘዙ መድኃኒቶችን ግን በሆስፒታሉ ውስጥ ባለማግኘታቸው ከግል መድኃኒት መደብር ሲገዙ ነው የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ያገኛቸው፡፡
በሚኖሩበት አካባቢም መድኃኒት በሆስፒታል ስለማይገኝ ከውጭ በመግዛት ተጨማሪ ወጭ እንደሚያወጡ እና ገንዘብም እንደማይመለስላቸው አንስተዋል፡፡ በመንግሥት ጤና ተቋማት ያለው የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እንዲፈታም ጠይቀዋል፡፡
በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል የፋርማሲ ግብዓት አስተባባሪ ይኸነው አጥናፉ ሆስፒታሉ በዓመት 560 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ መድኃኒቶች ቢያስፈልጉትም በበጀት እጥረት ምክንያት ማሟላት አልተቻለም ብለዋል።
የተቋሙ የውስጥ ገቢ ከ280 ሚሊዮን ብር የማይበልጥ በመኾኑ መድኃኒቶችን በሙሉ አቅም ለመግዛት አልተቻለም፤ የአቅርቦት መጓተትም ሌላው ችግር እንደኾነ አንስተዋል፡፡ ከመንግሥት የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ጋር የ228 ሚሊዮን ብር ውል መኖሩን ገልጸዋል። እስካሁን የቀረበው 22በመቶ ብቻ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
የመድኃኒት ዋጋ መጨመር የሚገዛውን መጠን እንደቀነሰውም ተናግረዋል፡፡ ከሚፈለገው መድኃኒት የቀረበው 48 በመቶ ብቻ ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ታካሚዎች 80 በመቶ መድኃኒት በሆስፒታሉ አግኝተዋል፤ ዘንድሮ ግን ወደ 72 በመቶ ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል። መድኃኒቶች እንዳይባክኑ ዘመናዊ አሠራር መዘርጋቱንም ጠቁመዋል፡፡
የጤና መድኅን ክፍያዎችን በወቅቱ በመሠብሠብ እና ከጤና ቢሮ ጋር በመተባበር አቅርቦቱን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መኾኑን አመላክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የሰሜን ምዕራብ ክላስተር እና የባሕር ዳር ቅርንጫፍ አሥተባባሪ አምሳሉ ጫኔ በጤና ተቋማት እና በአቅራቢው መካከል ፍላጎትን መሠረት ያደረገ አዲስ አሠራር ተጀምሯል ብለዋል፡፡ ይህም በሁለቱም ወገኖች ላይ አስገዳጅነት እና ተጠያቂነትን እንደሚጥል አስረድተዋል።
በአሠራሩም የጤና ተቋማት ፍላጎታቸውን በጤና ቢሮ በኩል ያሳውቃሉ፤ አቅራቢው ደግሞ በውሉ መሠረት በየሩብ ዓመቱ መድኃኒት ያቀርባል ነው ያሉት። አቅራቢው ማቅረብ ካልቻለ፣ ተቋማቱ ከሌላ ቦታ እንዲገዙ የፈቃድ ደብዳቤ እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ ለማቅረብ ካቀዳቸው መድኃኒቶች እስካሁን ማቅረብ የቻለው በአይነት 88 በመቶ በመጠን ደግሞ 42 በመቶ ብቻ እንደኾነ ገልጸዋል። ምክንያቱ ደግሞ የጤና ተቋማት ያለባቸው የበጀት እጥረት እና የፍላጎት መጠን አለመስተካከል እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡ የግዥ ፍላጎትም ዘግይቶ በመድረሱ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የአቅርቦት መጓተት እንደፈጠረ አንስተዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ተቋማት ፍላጎታቸውን ቀድመው እንዲያሳውቁ፣ የግዥ ሥርዓቱ እንዲጠናከር እና ድርጅቱ የማያቀርባቸውን መድኃኒቶች በሌሎች የግል አቅራቢዎች እንዲሟሉ የማመቻቸት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦት፣ ስርጭት እና ክትትል ዳይሬክተር ዘለቀ አበጀ የጤና ተቋማት ከውስጥ ገቢያቸው ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚኾነውን ለመድኃኒት ግዥ እንዲመድቡ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ነገር ግን የበጀት እጥረት ችግር እንደኾነባቸው ነው የገለጹት፡፡ ብክነትን ለመቀነስ ሲባል የተዘረጋው ሥርዓት አዲስ በመኾኑ በመድኃኒት አቅርቦት ላይ ክፍተት መኖሩንም ተናግረዋል፡፡
ሙሉ ፍላጎታቸውን ማግኘት የቻሉት ተቋማት ከ40 በመቶ እንደማይበልጡም አስረድተዋል፡፡
በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት 86 በመቶ ታካሚዎች የሚፈልጉትን መድኃኒት በጤና ተቋማት ውስጥ ማግኘት ችለዋል። ይህም ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የተሻለ አፈጻጸም እንደኾነ ገልጸዋል።
የአቅርቦት ክፍተቶችን ለመሙላት የበጀት ድጎማ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ በነፃ ለሚሰጡ ሕክምናዎች የሚወጡ መድኃኒቶችን የመተካት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ ለወደፊት የመድኃኒት አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በትብብር ይሠራል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
