
ባሕር ዳር: የካቲት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ አራት ሞዴል ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ነው።
እየተገነቡ የሚገኙት ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።
በፍኖተ ሰላም ከተማ የሚገነባው ሞዴል ትምህርት ቤት የክልሉ የትምህርት መሠረተ ልማትን ለማዘመን ከታሰቡት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው።
የፍኖተ ሰላም ሞዴል ትምህርት ቤት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኀይለ ገብርኤል አድማሱ ግንባታው መስከረም 10/2018 ዓ.ም መጀመሩን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ግንባታው 36 በመቶ ላይ ደርሷል ነው ያሉት፡፡በተያዘው ዓመት መጨረሻ በማጠናቀቅ በ2019 ዓ.ም መስከረም ወር ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ የአሥተዳደር ሕንጻ፣ ሁለት ዘመናዊ ቤተ ሙከራዎች፣ እያንዳንዳቸው 10 የመማሪያ ክፍሎች ያሏቸው አራት የመማሪያ ብሎኮች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ ካፍቴሪያ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ክሊኒክ፣ የስፖርት ሜዳዎች (እግር ኳስ፣ እጅ ኳስ እና ባስኬት ቦል) እና ሌሎች አስፈላጊ መገልገያዎችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡
በአንድ ክፍል 40 ተማሪዎችን በመቀበል እስከ 1 ሺህ 600 ተማሪዎችን የማስተማር አቅም እንዳለውም ተጠቅሷል፡፡
በመጀመሪያ ዙር በ2019 ዓ.ም አንድ ሺህ የሚደርሱ የ9ኛ ክፍል ተማሪዎችን በመቀበል ሥራ ለማስጀመር መታቀዱንም ገልጸዋል።
የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደረጀ ታደሰ ከ505 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የሚገነባው ይህ ትምህርት ቤት በዞኑ ያሉ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ልምድ ሊወስዱ የሚችሉበት እንደሚኾን ገልጸዋል፡፡ ለቀጣይ ዓመት የመምህራን እና የሌሎች ሰው ኀይሎች ቅጥር በጀት ለማስያዝ ዝግጅት መጀመሩንም አመልክተዋል፡፡
በአማራ ትምህርት ቢሮ የሲቪል ምህንድስና ዳይሬክተር ሚካኤል ንብረት እንዳሉት በክልሉ ባሉ አራት ከተሞች ላይ ጥራታቸውን የጠበቁ ሞዴል ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ነው፡፡
ከፍኖተ ሰላም ከተማ ሞዴል ትምህርት ቤት በተጨማሪ በደብረ ማርቆስ ከተማ በ486 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ ያለው ሞዴል ትምህርት ቤት 15 ነጥብ 19 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት።
በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ በ561 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ ያለው ደግሞ 30 በመቶ ደርሷል ተብሏል። በደቡብ ወሎ ዞን መቅደላ ወረዳ በ501 ሚሊዮን ብር ወጪ በግንባታ ላይ ያለው ሞዴል ትምህርት ቤት 37 ነጥብ 23 በመቶ ደርሷል ብለዋል፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተደረገባቸው ሲኾኑ በፌደራል መንግሥት ድጋፍ እየተገነቡ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ሞዴል ትምህርት ቤቶቹ የተሟላ መሠረተ ልማት እና ዘመናዊ መገልገያዎችን በመያዝ የተማሪዎች ውጤትን ለማሻሻል ትልቅ አቅም እንደሚኖራቸው ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
