
ባሕር ዳር፡ የካቲት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የስድስት ወር አፈጻጸሙን በደብረ ብርሃን ከተማ እየገመገመ ነው።
የቢሮው ምክትል ኀላፊ ካሳ አበባው ለአሚኮ እንደተናገሩት ቢሮው የሰው ሃብትን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመምራትና ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ቀልጣፋ የገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን እየተገነባ ይገኛል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ በባሕር ዳር ከተማ ሁለት፣ በደሴ ከተማ አንድ፣ በአጠቃላይ ሦስት የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገንብቶ በሥራ ላይ ነው ብለዋል። እስካሁንም በእነዚህ ማዕከላት ከ30 ሺህ በላይ ተገልጋዮች መስተናገዳቸውን ተናግረዋል።
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በአራት ከተሞች ላይ ሙሉ መዋቅር ተሠርቶለት ወደ ተግባር መገባቱንም አብራርተዋል።
ወልድያ፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ታቦር፣ ኮምቦልቻ እና ደብረ ማርቆስ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በቀጣይ የሚያስጀምሩ ከተሞች መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 14 ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ ነው፣ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ የፌዴራል ተቋማት ናቸው።
ዘጋቢ፦ ብርቱካን ማሞ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
