
ገንዳ ውኃ፡ የካቲት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ሙላት እሱባለው እና ወይዘሮ አዳኑ በላይ የአዳኝ ሀገር ጫቆ ወረዳ እና የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው።
ሁለቱንም ወላጆች አሚኮ ያገኛቸው ልጆቻቸውን በመተማ ጠቅላላ ሆስፒታል ለማሳከም መጥተው ነው።
ወላጆቹ እንዳሉት ልጆቹ ከፍተኛ ሙቀት ሲያሳዩ፣ የማልቀስ ጸባይ ሲያሳዩ እና ጉሮሯቸው ሲቀላ ቶንሲል ሊኾን እንደሚችል ወደ ጤና ተቋም ለማሳከም እንደመጡ ተናግረዋል።
ልጆቹ በተደረገላቸው ሕክምና የቶንሲል በሽታ እንዳመማቸው መረጋገጡን ወላጆች ገልጸዋል።
ልጆቹ ሕክምናውን ካገኙ በኋላ የሚሰማቸው ስሜት እና ሕመም እንደቀነሰላቸውም ተናግረዋል። ልጆች የቶንሲል በሽታ ምልክት ሲያሳዩ ወደ ሕክምና መውሰድ እንደሚገባም ይመክራሉ።
የቶንሲል በሽታ በባክቴሪያ እና በቫይረስ ሳቢያ የሚከሰት የጤና ችግር ሲኾን በአብዛኛው ከአምስት እስከ 10 ዓመት የዕድሜ ክልል ያሉ ሕጻናትን የሚያጠቃ የበሽታ አይነት መኾኑን በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ጠቅላላ ሆስፒታል የሕጻናት ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ናትናኤል አለፈ ተናግረዋል።
በበሽታው ተጠቂ የኾነ ሰው በዘጠኝ ቀናቶች ውስጥ ሕክምና ማግኘት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የድካም ስሜት ከተሰማ፣ ምግብ አላስውጥ ካለ፣ ጡት አላስጠባ ካለ፣ ከፍተኛ ሙቀት ካለ፣ ለመተንፈስ መቸገር ካለ፣ ጉሮሮ መግል ከያዘ፣ ዐይን ከቀላ፣ ፀባይ የሚነሳ እና በቀኝ እና በግራ ጉሮሮ የሚያብጥ ከኾነ የቶንሲል በሽታ ስለሚኾን በአቅራቢያ ወደ አለ ጤና ተቋም በመሄድ መታከም እንደሚገባም ዶክተሩ መክረዋል።
እንደ ዶክተሩ ገለጻ የቶንሲል በሽታ በአግባቡ ካልታከመ እንደ ልብ እና የኩላሊት ሕመም፣ ለጨጓራ እና ለሥነ አዕምሮ ችግር እና መሰል ተጓዳኝ በሽታዎች እንደሚያጋልጥም አብራርተዋል።
ከዚህ ባለፈም ለሞት የሚዳርግ በሽታ መኾኑንም ጠቁመዋል።
በቶንሲል የታመመ ሰው መካከለኛ በኾነ መንገድ የቀዘቀዘ በረዶ፣ ጁስ፣ ውኃ፣ ሻይ፣ አጥሚት እና ሾርባ መጠቀም ይኖርበታል ብለዋል።
በተደጋጋሚ ኢንፌክሽኑን ለሚያመጡ ጀርሞች ልጆች እንዳይጋለጡ በሳሙና እጅ እና ሰውነታቸውን ማጠብ፣ ትምህርት ቤት የሚውሉ ሕጻናትን ከአቻዎቻቸው ጋር ያላቸውን የቀረበ ግንኙነት በመቀነስ በቫይረሶች እና በቫክቴሪያዎች በቀላሉ እንዳይጋለጡ ማድረግ እና ከተለያዩ መጥፎ ሽታ ካላቸው ነገሮች በመጠበቅ የቶሲልን በሽታ መከላከል እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
በማኅበረሰቡ ዘንድ እንጥል መቁረጥ የቶንሲል በሽታን ይከላከላል ተብሎ የሚታሰበው የተሳሳተ አመለካከት እንደኾነ እና ይህ ጎጂ ድርጊት መቆም እንዳለበት ዶክተር ናትናኤል አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
