ተማሪዎችን ለሀገር እና ለክልል አቀፍ ፈተናዎች ብቁ ለማድረግ እየተሠራ ነው።

11

 

ደብረማርቆስ፡ የካቲት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ የጎጃም በር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ቤዛዊት መንግሥቴ ትምህርት ቀጣይ ሕይወቴን መስመር የማስይዝበት ዓላማየ ነው ትላለች።

ተማሪዋ ለትምህርቷ በምትሰጠው ልዩ ትኩረት እና በትምህርት ቤቱ በሚደረግላቸው ተጨማሪ እገዛ በሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አቅዳ እያጠናች ነው።

የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችም ኤፍራታ ከፋለ እና ተማሪ ቴዎድሮስ እንቢአለ ባለፈው ዓመት ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት ተመርጠው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ እየተደረገላቸው ባለው ልዩ ድጋፍ የሚሰጣቸውን ክልላዊ ፈተና በጥሩ ውጤት በማለፍ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመቀላቀል ዝግጅት እያደረጉ ነው።

የትምህርት ቤቱ መምህራንም ተማሪዎች ለክፍል ደረጃው የሚጠበቀውን ዕውቀት እና ክህሎት እንዲጨብጡ የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣት ላይ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ተማሪዎች ያለባቸውን የዕውቀት ክፍተት በምዘና ለይተው በመሙላት ለሀገር እና ለክልል አቀፍ ፈተናዎች ብቁ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መኾኑንም አስገንዝበዋል።

የደጀን ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተገኔ ኪዳነማርያም ትምህርት ቤቶችን በተለያዩ ግብዓቶች በመደገፍ ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ የማድረግ ሥራ በማከናወን የሀገር አቀፍ እና የክልል አቀፍ ተማሪዎች የማለፊያ ነጥብ አሟልተው እንዲገኙ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጌታሁን ፈንቴ ከመደበኛው የትምህርት ጊዜ በተጨማሪ ሌሎች ተጓዳኝ አማራጮችን በመጠቀም ተማሪዎችን ለፈተና በማዘጋጀት የተመዘገቡ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ በቁጭት መሥራት ይገባል ብለዋል።

በዞኑ 41 ትምህርት ቤቶች የሀገር አቀፍ እንዲሁም 191 ትምህርት ቤቶች ክልል አቀፍ ፈተና እንደሚያስፈትኑም ተገልጿል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሂደት የሚገነባ ነው።
Next articleበሕገ ወጥ ድርጊታቸው በቀጠሉ ጽንፈኞች ላይ የሚደረገው ሕግ የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የምሥራቅ ዕዝ አስታወቀ።