
ባሕር ዳር: የካቲት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተሟላ የጤና አገልግሎት ማግኘት ለአዳርቃይ ወረዳ ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ኾኖ ቆይቷል። መንግሥትም ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት በወረዳው የሆስፒታል ግንባታ አከናውኗል። ነገር ግን ሆስፒታሉ በመጠናቀቅ ላይ እያለ በሰሜኑ ጦርነት በመውደሙ ወደ ሥራ መግባት አልቻለም።
ዲያቆን አበበ ሞላዬ በሰሜን ጎንደር ዞን የአዳርቃይ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። በ2017 ዓ.ም በወሊድ ምክንያት ባለቤታቸውን በሞት አጥተዋል።
የአዳርቃይ ጤና ጣቢያ የወሊድ አገልግሎቱን መስጠት ባለመቻሉ ወደ ደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል ሪፈር ተጽፎላቸው በጉዞ ላይ እንዳሉ ባለቤታቸውን በሞት እንደተነጠቁ ነግረውናል።
የአዳርቃይ ሆስፒታል በጦርነቱ መውደሙ እና ወደ ሥራ አለመግባቱ ለዚህ ሁሉ ምክንያት መኾኑን ገልጸው ሌሎችም ነዋሪዎች እየተቸገሩ ስለመኾኑ አብራርተዋል።
የአዳርቃይ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሳምሶን በቀለ ሆስፒታሉ ግንባታ በጦርነቱ ከመውደሙ በፊት በ2013 ዓ.ም 92 በመቶ ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል። በህወሃት ከፍተኛ ውድመት ከደረሰበት በኋላ መልሶ ግንባታ ሳይከናወንለት መቆየቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም በሪፈራል ሥርዓት ማኅበረሰቡ ለእንግልት እና ላልተፈለገ ወጭ እየተዳረገ ነው ብለዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍም የክልሉ መንግሥት በ2017 ዓ.ም የሆስፒታሉን መልሶ ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ በ 27 ሚሊየን ብር በተመረጡ 5 ብሎኮች የበር እና መስኮት፣ የጣራ እና ኮርኒስ፣ የቀለም እና መሰል ግንባታዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል።
ጤና ሚኒስቴርም የማኅበረሰቡን ችግር በመረዳት ቀሪውን ሥራ በአፋጣኝ ለማጠናቀቅ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ብለው በተስፋ እየጠበቁ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ልዑል ብርሃን እንዳሉት ሆስፒታሉ ወደ ሥራ ባለመግባቱ ከ500 ሺህ በላይ የአዳርቃይ፣ የጠለምት፣ የምሥራቅ ጠለምት እና የምዕራብ ጠለምት ነዋሪዎች በተሟላ ሕክምና እጦት ችግር ውስጥ እንዲኾኑ አድርጓል።
በአካባቢው በወር በትንሹ 30 የሚደርሱ እናቶች ለወሊድ ወደ ደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል እንደሚላኩም ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ገስጥ ጥላሁን የአዳርቃይ ሆስፒታል ሳይጠናቀቅ በጦርነቱ ውድመት እንደደረሰበት ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት በ 27 ሚሊየን ብር ከደረሰበት ውድመት የተወሰነውን ክፍል መልሶ ግንባታ እያከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።
የሆስፒታሉን ውድመት ለፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስተላልፈው እንደነበር የጠቀሱት አቶ ገስጥ መልሶ ግንባታው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከያዛቸው ግንባታዎች መካከል እንደኾነ ነው የነገሩን።
ጠቅላላ የደረሰበትን ጉዳት ተጠግኖ አገልግሎት እንዲጀምር ለማድረግ ቢሮው እየሠራ ካለው በተጨማሪ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ገብቶ ጠቅላላ ጉዳቱንም፣ ያልተጠናቀቁ ሥራዎችንም ለማጠናቀቅ የጨረታ ሥራውን ጨርሷል፤ ውል እየሰጠም ይገኛል፤ ከመጪው መጋቢት ወር ጀምሮ ወደ ግንባታ ይገባል ብለዋል።
ውሉ የሚያዘው ከአራት እስከ ስድስት ወራት ለማጠናቀቅ ነው ያሉት የቢሮው ምክትል ኀላፊ በሥድስት ወራት ውስጥ መልሶ ግንባታው ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
