ምርጫ ነክ መረጃዎች ተዛብተው እና አሳሳች ኾነው እንዳይቀርቡ ጥረት እየተደረገ ነው።

10

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በያዝነው ሳምንት በምርጫ እና በድኅረ ምርጫ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ምርጫ ነክ ሐሰተኛ እና አደናጋሪ መረጃዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችለውን የብሔራዊ ትብብር ስምምነት ይፋ አድርጓል።

በይፋ ማድረጊያ መድረኩ ላይ የተገኙት የቦርዱ ሠብሣቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ የትብብር ማዕቀፉ ቦርዱ መጭው ምርጫ ነፃ እና ተአማኒ እንዲኾን፤ ምርጫ ነክ መረጃዎች ተዛብተው እና አሳሳች ኾነው ለኀብረተሰቡ እንዳይቀርቡ ብሎም የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተአማኒነት ተጠብቆ እንዲከናወን ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራበት ነው ብለዋል።

ቦርዱ ምርጫን በገለልተኝነት፣ በነፃነት እና በታማኝነት ለማካሄድ የተቋቋመ ሕገ-መንግሥታዊ ተቋም መኾኑን ያስታወሱት የቦርዱ ሠብሣቢ የትብብር ስምምነቱ ቦርዱ ሐሰተኛ እና አደናጋሪ መረጃዎችን በመከላከል በምርጫው ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያደርሱ የሚያደርገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የብሔራዊ ትብብር ስምምነቱ ዓላማ በምርጫ ሂደት ሊሠራጩ የሚችሉ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለማጣራት፤ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት፤ መራጮች እና በምርጫው በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ድርሻ ያላቸውን ተቋማት እና ግለሰቦች በተዛባ መረጃ ላይ ከተመሠረተ ውሳኔ አሰጣጥ እንዲጠበቁ ለማድረግ እና ምርጫው ነፃ እና ተአማኒ መኾኑን ለማረጋገጥ ያለመ ነው።

ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (ዩኤንዲፒ) ጋር በመተባበር በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ የልማት ድርጅቱ የአፍሪካ ተወካይ ሳሙኤል ዶ (ዶ.ር) የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ የምርጫን ተአማኒነትን አደጋ ላይ ከመጣልም በተጨማሪ ግጭት የሚያስነሱ እንደኾኑ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለሰባተኛ ጊዜ የምታካሂደው ጠቅላላ ምርጫ ተአማኒነቱ የሚረጋገጠው በምርጫ ጣቢያ ከሚተገበረው የምርጫ ሂደት በተጨማሪ ለዜጎች እና በምርጫው ተሳታፊ ለኾኑ ግለሰቦች እና ተቋማት በሚደርሰው ዕውነተኛ የምርጫ መረጃ ነው ብለዋል።

በመድረኩ ላይ አጠቃላይ የብሔራዊ ትብብር ሥራው ዕቅድ እና ተጠባቂ ውጤትን የተመለከተ ገለጻ ተሰጥቷል።

የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮዎችም ቀርበው ውይይት ስለመደረጉ ከምርጫ ቦርዱ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፕላስቲክ ምርቶችን ከመጠቀም የሚከለክለው አዋጅ ምን ምን ጉዳዮችን ይዞ ይኾን?
Next articleበጦርነት የወደመው የአዳርቃይ ሆስፒታል ሙሉ ጥገና ሊደረግለት ነው።