
ባሕር ዳር፡ የካቲት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለ19 ዓመታት ያህል ስትጠቀምበት የነበረውን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ የሚያትተውን አዋጅ አሻሽላ በአዲስ አዋጅ ተክታለች። አዋጅ ቁጥር 513/1999 ተብሎ ሲጠራ የነበረው አዋጅ በአዲሱ 1383/2017 ተተክቷል።
ይህ አዋጅ ባለፈው ዓመት በሚኒስትሮች ምክርቤት ፀድቆ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተላለፈ በኋላ ከጥር 23/2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።
ይህ አዋጅ ሲወጣ በርካታ ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገ ሲኾን በዋናነት ከፕላስቲክ ምርቶች ጋር በተያያዘ ትልቅ ትኩረት ስለመስጠቱ የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ያነሳል። በባለሥልጣኑ የአካባቢ እና አየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አወቀ ይታይህ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስረዱት የቀደመው አዋጅ ከአካባቢ ደኅንነት እና ቁጥጥር ላይ እዚህ ግባ የሚባል ትኩረት አልሰጠም ነበር ብለዋል።
ይሁን እና አሁን ላይ የወጣው አዋጅ ቁጥር 1383/2017 ጥብቅ የኾነ የአካባቢ ደኅንነት እና ቁጥጥር ስለማስቀመጡ አስረድተዋል።
👉በአዋጁ ከፕላስቲክ ምርቶች ጋር የተያያዙ ነጥቦች እንዴት ታዩ?
አቶ አወቀ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት በሰጠችው ከፍተኛ ትኩረት ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶችን ከልክላለች ብለዋል። ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶችን ማምረት ማከፋፈል እና አለፍ ሲልም ሲጠቀሙ መገኘት የሕግ ተጠያቂነትን ያስከትላሉ ብለዋል። እነኝህ የፕላስቲክ ምርቶች በዕለት ከዕለት የሕይወት መስተጋብር የምንጠቀምባቸው እና በየግብይት ማዕከላት የሚገኙ ስስ ፕላስቲኮችን ያጠቃልላል ነው ያሉት።
👉የሕግ መተላለፍ እና ተጠያቂነት…?
አሠራሮችን ወደ ጎን በመተው ጥፋት የፈፀሙ ግለሰቦች በዝቀተኛው ደረጃ ከ2ሺህ ብር የሚጀምር የገንዘብ መቀጮ ይጣልባቸዋል ብለዋል አቶ አወቀ። በመካከለኛ ነጋዴዎች እና አከፋፋዮች ከ50 ሺህ እስከ 200ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይጣላል ያሉት አቶ አወቀ በሦሥተኛ ደረጃ አምራቾች ደግሞ በደረጃ ሁለት የተቀመጡትን መቀጮ በእጥፍ እንዲተላለፍባቸው ያስገድዳልም ብለዋል።
👉በአማራ ክልል የአዋጁ አፈፃፀም…..?
አዋጁ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ መኾን ጀምሯል። በክልሉ በሚገኙ ከፍተኛ ከተሞች የግንዛቤ ፈጠራን ጨምሮ ሌሎች ተግባራት ተከናውነዋል። አሁን ላይ የአፈፃፀም ክፍተት ቢኖርም አዋጁ ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ጥረት እየተደረገ ነው። ለአዋጁ ተፈፃሚነትም የጋራ ጥረትን ይጠይቃል ነው የተባለው።
👉ፕላስቲክን በምን እንተካ….?
አሚኮ በዚህ ጉዳይ ላይ የጠየቃቸው አቶ አወቀ በክልሉ የሚገኙ የጨርቃጨርቅ አምራች ፋብሪካዎች እና ኢንተርፕራይዞች ተኪ ምርቶችን ለማምረት ወደ ተግባር ገብተዋል ብለዋል። ይሁን እና ምርቱ በበቂ ሁኔታ እየቀረበ አይደለም ያሉት አቶ አወቀ ዳግም ጥቅም የሚሰጡ የተለያዩ ከረጢቶችን ኅብረተሰቡ አዘጋጅቶም ቢኾን መጠቀም ይገባዋል ብለዋል።
👉ፕላስቲክን ለምን እናስወግደዋለን?
የፕላስቲክ ምርት በዓለም አካባቢ በካይ ከኾኑት ምርቶች መካከል ዋነኛው በመኾኑ በኅብረተሰብ ጤና ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ከፍተኛ መኾኑ ሌላኛው ምክንያት ነው። ከቅጣትም በላይ ጤና የሚቀድም በመኾኑ ፔስታልን አለመጠቀም ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
