የዳንግላ-ጃዊ አስፋልት መንገድ ሥራ ለምን ተቋረጠ?

11

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአስፋልት መንገዶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ሲጠናቀቁ መንገዱ ለተሠራለት አካባቢ ማኅበረሰብ ሰፊ ግልጋሎት ከመስጠት ባሻገር ሀገርን ከተጨማሪ ወጭ የማዳን ጉልህ ድርሻ አላቸው።

ኾኖም ግን በተለያዩ ምክንያቶችን በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ያለመጠናቀቅ፤ ከፊሎች ደግሞ በጊዜያዊነት የሚቋረጡባቸው አጋጣሚዎች ይስተዋላሉ።

አሁን ላይ የግንባታ ሥራቸው ከተቋረጡ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከልም የዳንግላ- ጃዊ አስፋልት መንገድ አንዱ ነው።

ይህ 73 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአስፋልት መንገድ ሥራ በ2013 ዓ.ም ነበር ሥራ የጀመረው። ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞለትም ነበር። በሦስት ዓመት ተኩል ገንብቶ ለማጠናቀቅ ታቅዶም ነበር። ይሁን እንጅ ከአምስት ዓመት በላይ ኾኖታል። ዛሬም አልተጠናቀቀም።

አሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ያነጋገራቸው የጃዊ አካባቢ ነዋሪ አወቀ ስንታየሁ የዳንግላ እና ጃዊ አካባቢ ማኅበረሰብ የረጅም ዓመት ጥያቄ የነበረው የአስፋልት መንገድ ሥራ ሲጀመር ከፍተኛ ደስታ ፈጥሮላቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ጅማሮውም ጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ እንደነበረው ነው የጠቀሱት። አሁን ላይ ግን የመንገድ ሥራው ሙሉ በሙሉ ቆሟል ብለዋል።

የአስፋልት ንጣፍ ብቻ የቀረው ውስን ኪሎ ሜትር መንገድም በክረምት ጎርፍ እና በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት እንደደረሰበት ተናግረዋል። ቀሪው መንገድም ጥገና እየተደረገለት ስላልኾነ ለትራንስፖርት እንቅስቃሴ አስቸጋሪ እንደኾነ አንስተዋል።

ከባሕር ዳር ወደ ጃዊ የሚመጡ ሸቀጣ ሸቀጦች እና ሌሎች የፍጆታ እቃዎች አቋራጭ በኾነው ዳንግላ- ጃዊ ለመምጣት አስቸጋሪ በመኾኑ በኮሶበር-ቻግኒ-ጃዊ መንገድ ለመምጣት አስገዳጅ ኾኗል ነው ያሉት። ይህም የኑሮ ውድነቱን አባብሷል፤ የፍጆታ እቃዎች የአቅርቦት እጥረት እንዲኖር አድርጓል ብለዋል።

አካባቢው በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አበርክቶ ያላቸው የአኩሪ አተር፣ የለውዝ፣ የሰሊጥ እና ሌሎች ምርቶች በስፋት የሚመረትበት መኾኑንም አመላክተዋል።

ኾኖም ግን ጣና በለስን ጨምሮ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ድርጅቶች እና የአካባቢው አርሶ አደሮች ያመረቷቸውን ምርቶች ለገብያ ለማቅረብ አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ነው የገለጹት። ለተሻለ ሕክምና ወደ ባሕር ዳር በሪፈር የሚላኩ እናቶች ላይም እንግልት ፈጥሯል ብለዋል።

መንገዱ የተሽከርካሪ እቃዎችን እየሠበረ የተሽከርካሪ ባለቤቶችን ላልተፈለገ ወጭ መዳረጉንም አንስተዋል። መንገዱ በተቀመጠለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ኅብረተሰቡ ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ በቃል የሚገለጽ እንዳልኾነ ነው የተናገሩት። የጸጥታ ሁኔታውን እንደ ምክንያት መጠቀም ግን ተገቢነት እንደሌለው ነው የገለጹት።

ማኅበረሰቡ የፕሮጀክቱን የግንባታ ግብዓቶችን እና ማሽነሪዎች በባለቤትነት አሁንም እየጠበቀ ለመንገዱ መሠራት ያለውን ፍላጎት አሳይቷል ብለዋል። መንገዱ በፍጥነት ተሠርቶ ለአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጥ እና ችግሮችን እንዲያቀልም ጠይቀዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቱን እየተከታተለ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር በበኩሉ የመንገድ ፕሮጀክቱ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በአካባቢው በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ሙሉ በሙሉ መቆሙን ከአሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ጋር በነበረው ቆይታ መረጃ አጋርቷል።

የጸጥታ ችግሩ እስከ ተፈጠረበት ጊዜ ድረስ በነበረው የሥራ እንቅስቃሴ 20 በመቶ አካባቢ አፈጻጸም እንደነበረውም ተቋሙ ገልጿል።

አሚኮ ዲጅታል ሚዲያ የጸጥታ ችግሩ ብቻ መንገድ ሥራው ሙሉ በሙሉ እንዲቆም አድርጎታል ወይ? በአካባቢው ነዋሪ በኩል የጸጥታ ችግሩ እንደ ምክንያት ሊወሰድ አይገባም የሚል ሀሳብ ተነስቷል በሚል ላነሳው ጥያቄም ሌሎች ምክንያቶች አለመኖራቸውን ነው የጠቀሰው። ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር በሌለበት ጊዜ ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅም ይሠራ ነበር ነው ያለው ተቋሙ።

የጸጥታ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት ሥራውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ ሲደረግ እንደነበርም አንስቷል።
አሁን ላይ ግን መቀጠል አልቻለም ብሏል ነው ያለው።

አልፎ አልፎ አሁንም የጸጥታ ችግር እንደሚስተዋል መረጃው አለን ብሏል ተቋሙ። መንገዱ የማኅበረሰቡ የረጅም ዓመት ጥያቄ ስለኾነ እና መገንባት ስላለበት እንደገና የግንባታ ሥራውን ለመጀመር እና የጥገና ሥራዎችን ለመሥራት በተደጋጋሚ ውይይት እየተደረገ መኾኑንም አሳውቋል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ምንድን ነው? መቼስ ይጠናቀቃል በሚል አሚኮ ላቀረበው ጥያቄ በቅርብ እንደሚጀመር ከመግለጽ ባለፈ ቁርጥ ያለ የሚጀመርበት እና የሚጠናቀቅበትን የተረጋገጠ ጊዜ ተቋሙ ከመግለጽ ተቆጥቧል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ አለመጠናቀቁ ደግሞ ሀገርን ለተጨማሪ ወጭ እንደሚዳርግ ነው የጠቀሰው።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየእስራኤሉ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ።
Next articleየፕላስቲክ ምርቶችን ከመጠቀም የሚከለክለው አዋጅ ምን ምን ጉዳዮችን ይዞ ይኾን?