በችግር ውስጥ ላለው ትምህርት የማኅበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መፍትሔ ነው።

2

 

ደብረ ማርቆስ: የካቲት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ በመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት የነበረውን አጠቃላይ አፈጻጸም ከባለድሻ አካላት ጋር ገምግሟል።

የደጀን ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተገኔ ኪዳነማርያም በወረዳው ካሉ 53 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በ38ቱ ትምህርት ቤቶች ላይ የመማር ማስተማር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቶችን በተለያዩ ግብዓቶች በመደገፍ ለመማር ማስተማር ምቹ የማድረግ ተግባርም በስፋት በማከናወን ሁሉም የተመዘገቡ ተማሪዎች ሳያቋርጡ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የሞጣ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተክሌ ጸዴ በዘርፉ ላይ ያጋጠሙ ማነቆዎችን ለይቶ በመፍታት በትምህርት ዘመኑ ለማስተማር በዕቅድ ከተያዘው ውስጥ 92 በመቶ የሚኾኑት ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ለትምህርት ጥራት፣ ግብዓት እና ተደራሽነት የአካባቢው ማኅበረሰብ ተሳትፎ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ የገለጹት ኀላፊው በመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ከባለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት መመዝገብ መቻሉን ነው የተናገሩት።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጌታሁን ፈንቴ በዞኑ ባለፉት ዓመታት ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ውጭ መኾናቸውን ገልጸዋል። በተለይ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት የተለየ ትኩረት በመስጠት ሕጻናት መሠረት እንዲይዙ የተለያዩ ተግባራት እየተሠሩ ነው ብለዋል።

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል ባለፈ ጉዳት የደረሠባቸውን መልሶ በመገንባት እና ተማሪዎችን በአግባቡ በማብቃት ትምህርትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ በውይይቱ ተመላክቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአካል ጉዳተኞች በምርጫ የመሳተፍ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል።
Next articleዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ምንድን ነው?