
ባሕር ዳር፡ የካቲት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈ እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ እንዲኾን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑ ተመላክቷል።
አካል ጉዳተኞች የመምረጥ፣ የመመረጥ እና በታዛቢነት የመሳተፍ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙም ጥሪ ቀርቧል።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የኾኑት ወይዘሮ ባንችአምላክ አቤ አይነ ስውር ሲኮኑ ቀደም ሲል በማኅበረሰቡ የተሳሳተ አመለካከት ምክንያት የአካል ጉዳተኞች በምርጫ የመሳተፍ ልምድ ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ አካል ጉዳተኝነት ከማንኛውም ተግባር እንደማያግድ በመረዳት መብትን ማስከበር እንደሚገባም ተናግረዋል።
ወይዘሮ ባንችአምላክ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ
ለመሳተፍ ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
“እኔ ዜጋ ነኝ፣ በመረጥኩት መመራት መብት አለብኝ” በሚል ስሜት እያንዳንዱ አካል ጉዳተኛ በነፃነት እና በንቃት መሳተፍ አለበት ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በቀጣይም ለአካል ጉዳተኞች እንደየጉዳት አይነታቸው ግንዛቤ የመፍጠር ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው የጠየቁት።
የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬሰላም ዘገዬ እንደገለጹት በክልሉ ከ4 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች ይገኛሉ። እነዚህ ዜጎች በምርጫው ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበርም 1ሺህ 150 አካል ጉዳተኞች በታዛቢነት እንዲመረጡም መደረጉን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም የአካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ዜጋ “ይወክለኛል፣ ይመራኛል” የሚሉትን ፓርቲ መምረጥ እና መመረጥ ይችላሉ፤ ለዚህም በንቃት መሳተፍ አለባቸው ብለዋል።
በመኾኑም አካታች ርዕዮተ ዓለም የሚያራምድ ፓርቲን በመምረጥ ሀገራዊ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ፣ ለዚህም በምዝገባ ወቅት ካርድ በማውጣት ዝግጁ እንዲኾኑ አሳስበዋል።
ለተፈጻሚነቱም የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲኾኑ እና ተገቢው አገልግሎት እንዲሰጥ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
