የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ደኅንነት ለመጠበቅ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ሕይወት መለወጥ ያስፈልጋል።

5

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የአይበገሬ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም የማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

የአይበገሬ ኑሮ ማሻሻያ እና ዘላቂ የሥነ ምህዳር ፕሮጀክት ከኬር ኢትዮጵያ እና ከአመልድ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በሰሜን ጎንደር ዞን በአራት ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 15 ቀበሌዎች ላለፉት 40 ወራት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱ ተነግሯል።

ለማኅበረሰቡ የገንዘብ ድጋፍ፣ የሥልጠና፣ የተሻሻሉ የሰብል ዘርያዎችን በማቅረብ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎችን በማከናወን የአካባቢውን ሥነ ምህዳር የመጠበቅ ብሎም የማኅበረሰቡን ሕይወት ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ መቆየቱም ተገልጿል።

የኬር ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማኅተመ ምክረ (ዶ.ር) ኬር ኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታት በክልሉ 10 ዞኖች የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሲፈጽም መቆየቱን ገልጸዋል።

ኬር ኢትዮጵያ ከአመልድ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በሰሜን ጎንደር ዞን በምግብ እና መጠጥ አቅርቦት፣ በሰብዓዊ እርዳታ፣ በሥልጠና፣ የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ እና በሌሎች ላይ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱንም ጠቅሰዋል።

አካባቢው በተፈጥሮ አደጋ የተጎዳ እና ትርፍ አምራች ባለመኾኑ በችግር ውስጥ የሚኖሩ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሕይወት ለማሻሻል ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

በተከናወነው ሥራም በተፈጥሮ ሃብት፣ በሰዎች ሕይወት እና በአመለካከት ተጨባጭ ለውጦች መጥተዋል ብለዋል።

የሰው ሕይወትም ተሻሽሎ ታይቷል ብለዋል። ኬር ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የአመልድ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዓለማየሁ ዋሴ (ዶ.ር) አመልድ ባለፉት 42 ዓመታት በዕለት እርዳታ፣ በመልሶ ማቋቋም፣ በዘላቂ ልማት እና በተለያዩ ተግባራት በተለይ በአማራ ክልል ሲሠራ የቆየ ሀገር በቀል ድርጅት መኾኑን አንስተዋል።

በዚህ ዓመትም በአራት ክልሎች በ118 ወረዳዎች 39 ፕሮጀክቶችን እንደሚያከናውን አሳውቀዋል። ፕሮጀክቱ ለማኅበረሰቡ አዳዲስ የአሠራር ዘዴዎችን አስተዋውቋል፤ የማኅበረሰቡን ሕይወትም አሻሽሏል ብለዋል።

ጎን ለጎንም የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ጉዳት ለመቀነስ የተቻለውን እንዳደረገ ገልጸዋል። ማኅበረሰቡን ከድህነት ለማውጣትም የድርጅቶቹ ሠራተኞች እና መሪዎች በብዙ ውጣ ውረድ ለሠሩት እና ለተደረገው የገንዘብ ድጋፍም አመሥግነዋል።

እስካሁን በነበረው ሥራ የነበሩ ክፍተቶችን በማረም እና ጥንካሬዎችን በማስቀጠል የማኅበረሰቡን ሕይወት ለማሻሻል እንደ ኬር ኢትዮጵያ ካሉ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መኾናቸውንም አሳውቀዋል።

የኦስትራያ የልማት ድርጅት ኀላፊ ሚካኤል ፊንክ የኦስትሪያ መንግሥት በኢትዮጵያ ለመተግበር ካቀዳቸው ተግባራት ውስጥ የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን መጠበቅ አንዱ እንደኾነ አሳውቀዋል።

ፓርኩ ዓለም አቀፍ በመኾኑ መጠበቅ እንዳለበትም ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ እና ፓርኩ ተያያዥ በመኾናቸው የማኅበረሰቡን ሕይወት በማሻሻል የፓርኩን ደኅንነት መጠበቅ አስፈላጊ እንደኾነም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ከኬር፣ ከአመልድ እና ከአይበገሬዎቹ ፕሮጀክቶቹ ጋር በትብብር ሠርተናል ነው ያሉት። ፕሮጀክቱ በአማራ ክልል ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለውጦችን አይተናል ነው ያሉት። የማኅበረሰቡ ተሳታፊነት እና ፕሮጀክቱን የያዘበትን መንገድም የሚደነቅ ነው ብለዋል።

አይበገሬነት በአጭር ጊዜ የሚመጣ አይደለም ያሉት ኀላፊው የኦስትሪያ የልማት ድርጅት ድጋፉን ይቀጥላል ብለዋል። በቀጣይም የገበያ ትስስር ላይ ትኩረት ለማድረግ እንዳሰቡ አመላክተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል። የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የተለያዩ ተጽዕኖዎች ያሉበት በመኾኑ ተጽዕኖውን ለመቀነስ እና በውስጡ ብሎም በዙሪያው የሚገኙ ነዋሪዎችን ሕይወት ለመቀየር የፕሮጀክቱ መግባት በጣም ጠቃሚ መኾኑንም አንስተዋል።

ፕሮጀክቱ በተጨባጭ 164 ሺህ የሚኾኑ የዞኑን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አረጋግጠዋል። ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ላይ በትኩረት መሥራቱንም ጠቅሰዋል። ማኅበረሰቡን በምጣኔ ሃብት ከመጥቀም ባሻገር በፓርኩ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ መቀነስም ችሏል ነው ያሉት።

ዞኑ ከፕሮጀክቱ መነሻ እና ተሞክሮ የሚኾን ስኬት አግኝቷል ያሉት አሥተዳዳሪው ፕሮጀክቱ ቀጠለም አልቀጠለም የተጀመረውን መልካም ጅምር የማስቀጠል እና የማስፋት ተግባር የአካባቢው መንግሥት መሪ እና የማኅበረሰቡ ኀላፊነት ይኾናል ብለዋል።

ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደብረታቦር ከተማ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
Next articleየአካል ጉዳተኞች በምርጫ የመሳተፍ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል።