“የዌስትፋሊያ መንገድ”

9

 

ባሕር ዳር: የካቲት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ቅዱስ የሮማ ግዛት” ወይንም የሮማ አጼ ግዛት ከ9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ በመካከለኛው አውሮፓ የነበረ ሥርዓት እንደኾነ ታሪክ ይነግረናል።

​ይህ ግዛት “ቅዱስ” ተብሎ የተሰየመበት ዋና ምክንያት ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጋር የነበረውን ጥብቅ ትስስር እና የቤተክርስቲያኗ ጠባቂ መኾኑን ለማብሰር ሲኾን “ሮማዊ” መባሉ ደግሞ ከ4 ምዕተ ዓመታት በፊት ፈርሶ የነበረውን ቀደምቱን የሮማ ግዛት ለመመለስ የታለመ እንደ ነበርም ይነገራል።

ግዛቱ እንደ ዘመናዊ ሀገራት አንድ ወጥ የኾነ ማዕከላዊ አሥተዳደር አልነበረውም። ይልቁንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ትናንሽ መሳፍንት እና ሃይማኖዊ ግዛቶች በሥምምነት የሚተሳሰሩበት የጥምረት ውጤት ነበር።

ግዛቱ በመካከለኛው ዘመን አውሮፓ ውስጥ ትልቅ የፖለቲካ ሚዛን ኾኖ ቢቆይም በውስጡ ባሉት ልዩነቶች እና በሃይማኖት መከፋፈል ምክንያት ዘላቂ አንድነትን አስጠብቆ መቀጠል አልቻለም።

በ16ኛው ክፍለ ዘመን የፕሮቴስታንት ሃይማኖት መነሳትን ተከትሎ ለ30 ዓመታት በአስከፊ ጦርነት ውስጥ እንዲገባ አደረገው እንጅ። ጦርነቱ ያስከተለው ደም መፋሰስ እና ውድመት በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ እጅግ ዘግናኝ ከኾኑ ምዕራፎች አንዱ ተደርጎም ይወሰዳል።

በእንጀባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ፍልስፍና መምህር ዓለምነህ አጋዤ እንደገለጹት ደግሞ የሮማን አጼ ግዛት የተለያዩ ግዛቶች በአንድ ላይ ተጨፍልቀው የተመሠረተ ግዛት ነበር። ግዛቱ ለረጅም ጊዜ ቢዘልቅም በ16ኛው ክፍለ ዘመን የፕሮቴስታንት እና ሌሎች ሃይማኖቶች ከካቶሊክ ሃይማኖት አፈንግጠው መውጣታቸውን ተከትሎ ከነባሩ ሃይማኖት ጋር ግጭት ውስጥ ገቡ ብለዋል።

ጦርነቱ በሂደት ከሃይማኖታዊ ባለፈ ወደ ግዛት፣ ሉዓላዊነት፣ ድንበር እና የመሳሰሉ ጉዳዮች እያደገ ለ30 ዓመታት ቀጠለ። 30 ዓመታት በተካሄደው ጦርነት የደረሰው ውድመት በአውሮፓ ታሪክ እጅግ ዘግናኝ ከኾኑ ምዕራፎች አንዱ መኾኑንም ነው የገለጹት።

ጦርነቱ የአሕጉሪቱን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ መዋቅር አፈራርሷል። ​ሙሉ መንደሮች እና ከተሞች ወድመዋል። ለዘመናት የገነቧቸው የባሕል እሴቶች ጋይተዋል። በረሃብ እና በተለያዩ ወረርሽኞች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። በሚሊዮን የሚቆጠሩት ሰዎች ደግሞ ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል።

ከዚህም በላይ የንግድ መስመሮች በመዘጋታቸው እና የገንዘብ ዋጋ በመውደቁ አውሮፓ በከፍተኛ የምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ውስጥ እንድትወድቅ አድርጓታል። ጦርነቱ ካስከተለው አካላዊ ጥፋት ባሻገር በሕዝቡ መካከል የተፈጠረው ሥነ ልቦናዊ ስብራት እና ጥልቅ የሃይማኖት ጥላቻ ለዓመታት የዘለቀ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።

በመጨረሻም ተፋላሚ ቡድኖች በተራዘመው ጦርነት አሸናፊ እና ተሸናፊ እንደሌለ ሲረዱ እ.ኤ.አ በ1648 በዌስትፋሊያ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ተገደዋል። የዊስትፋሊያ ውልም የተፈረመው ጀርመን ውስጥ በሚገኙት “ኦስናብሩክ” እና “ሙንስተር” ከተሞች ግንቦት 15/1648 እና ጥቅምት 24/1648 ነበር። ስምምነቱ በአንድ ጊዜ የተቋጨ ሳይኾን በተከታታይ የተካሄደ እንደነበርም ነው የገለጹት።

የዊስትፋሊያው ስምምነት ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?

የሠላም ስምምነቱ ዘመናዊቷ አውሮፓ እና የዛሬውን የዓለም ሥርዓት እንዲወለድ ምክንያት እንደኾነም ነው የጠቀሱት። አውሮፓ ​ከሃይማኖታዊ አሥተዳደር ወደ ፖለቲካዊ መዋቅር እንዲሸጋገር አድርጓል።

የአውሮፓ ነገሥታት ከሃይማኖት ይልቅ ለሀገራዊ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት የጀመሩት ከዚህ ስምምነት በኋላ መኾኑንም ነው የገለጹት። ዘመናዊ ድፕሎማሲ እንዲዳበር አድርጓል። ጦርነትን በድርድር እና በንግግር የመጨረስ ልምድ እንዲያድግ አድርጓል። የሃይማኖት እኩልነት እና ነጻነት ዕውቅና እንዲያገኝ ዕድል ፈጥሯል።

ይህም ከካቶሊክ ሃይማኖት ውጭ ሌላ ማምለክ እንደወንጀል ይቆጠር የነበረበት ጊዜ ቀርቶ እያንዳንዱ የአውሮፓ ንጉሥ ወይም መስፍን በግዛቱ ውስጥ የፈለገውን ሃይማኖት የመከተል እና የማስከተል መብት እንዲኖረው፣ በሌሎች ሀገራትም ዘንድ ይህ መብት እንዲተገበር ተወሰነ። ይህም ለዘመናት የዘለቀውን የሃይማኖት ጦርነት መንስኤ አስወገደ።

የሀገራት ሉዓላዊነት ጽንሰ ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕግ ደረጃ ዕውቅና አገኘ። ማንኛውም ሀገር በሌላው ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ፣ ድንበሮች እንዲከበሩ እና መንግሥታት በገዛ ግዛታቸው ላይ ፍጹም ሥልጣን እንዲኖራቸው የሚያስገድድ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ተዘረጋ።

ይህ ሥርዓት የሮማው ጳጳስም ኾኑ የሮማ አጼ ግዛት ንጉሠ ነገሥት በሌሎች ትናንሽ ሀገራት ላይ የነበራቸውን የበላይነት በመገደብ፣ ለዘመናዊው የዓለም የፖለቲካ ካርታ መሠረት ጥሏል።

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታም ከዌስትፋሊያ ታሪካዊ ስምምነት ጋር አዛምዶ መመልከቱ ተገቢ ነው። ከ380 ዓመታት በፊት በአውሮፓ የተከሰተው ያ አሰቃቂ እልቂት እና በመጨረሻ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ዛሬ ለኢትዮጵያም የሚሰጡት ታላላቅ ትምህርቶች አሉ። ​

በመጀመሪያ ደረጃ የዌስትፋሊያ ስምምነት የሚያስተምረው ትልቁ ቁም ነገር ጦርነት ድል አድራጊነት የሌለው አውዳሚ መንገድ መኾኑን ነው። ኢትዮጵያም አሁን ካለችበት የግጭት አዙሪት እንድትወጣ ከተፈለ የትኛውም ወገን በጠመንጃ አፈሙዝ ዘላቂ ሰላም እና አንድነትን ማምጣት እንደማይችል በመረዳት ለድርድር ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል።

​ሁለተኛው እና ዋናው ትምህርት ልዩነትን አምኖ መቀበል እና በመቻቻል መኖር ነው። በኢትዮጵያም ያለው ግጭት መፍትሔ ሊያገኝ የሚችለው የብሔር፣ የፖለቲካ እና የሐሳብ ልዩነቶችን በኃይል ለመድፈቅ ከመሞከር ይልቅ እያንዳንዱ ወገን የሌላውን ሕልውና፣ ማንነት እና መብት በሕግ እና በሥርዓት ዕውቅና ሲሰጥ ብቻ ነው።

“የእኔ እውነት ብቻ ይንገሥ” ከሚል አደገኛ አስተሳሰብ ወደ “የሁላችንም መብት ይከበር” ወደሚል የጋራ ስምምነት መድረስ እንደሚገባም አንስተዋል።

​ሌላኛው የዌስትፋሊያ ስምምነት ለኢትዮጵያ ትምህርት የሚኾነው ደግሞ ለሉዓላዊነት እና ለሕግ የበላይነት የሰጠው ዋጋ ነው።

በኢትዮጵያም ዘላቂ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው ከግለሰብ ፍላጎት በላይ ለሕግ የበላይነት ተገዥ በመኾን እና የዜጎችን እኩልነት በሚያረጋግጥ የጋራ የፖለቲካ ሥርዓት ላይ መስማማት ሲቻል ነው።

ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ የዌስትፋሊያ ስምምነት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት የሚያስተላልፈው መልዕክት በጦርነት ምክንያት የቱንም ያህል ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጥፋት ቢደርስ መጨረሻው ድርድር መኾኑን ነው።

የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ቀደሞ በመለየት በሰላማዊ መንገድ መፍታት ደግሞ ትልቁ ጥበብ ነው።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕገ ወጥ ንግድን ለመግታት ቅንጂታዊ አሠራርን ማጠናከር ይገባል።
Next articleበደብረታቦር ከተማ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።