የመንግሥት ሠራተኞች ለሰላም መስፈን፤ ለጋራ ልማት እና ተጠቃሚነት ሊሠሩ ይገባል።

6

 

ደብረ ማርቆስ: የካቲት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‌‎የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር‎” አገልጋይ የመንግሥት ሠራተኛ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

ውይይቱ በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት እና የመንግሥት ሠራተኞች በሀገረ መንግሥት ግንባታ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ የሚያነሳሳ ነው።

ተሳታፊዎቹ አሁን ላይ እያጋጠሙ ካሉ ችግሮች ለመውጣት የቆዩ እና የተዛቡ የታሪክ ትርክቶችን በማስተካከል ለጋራ ሰላም እና አንድነት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል።

የመንግሥት ሠራተኞች በአገልግሎት አሰጣጥም ኾነ በመልካም አሥተዳደር ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት ለመወጣት እንደሚሠሩ ነው የገለጹት።

በተለያዩ ሥልጠናዎች የሠራተኛውን አቅም በማሳደግ የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ መሥራት እንደሚገባም በተሳታፊዎቹ ተነስቷል።

በብልጽግና ፓርቲ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ መልካሙ ሽባባው የመንግሥት ሠራተኞች ለሰላም ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል። በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማሻሻልም ትኩረት መስጠት ይጠበቃል ብለዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ የመንግሥት ሠራተኞች ለሰላም መስፈን የመፍትሔ ሃሳቦችን በማንጸባረቅ ለጋራ ልማት እና ተጠቃሚነት ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ችግሮችን በውይይት መፍታት እና ለሃሳብ የበላይነት መገዛት እንደሚገባም አንስተዋል። ሠራተኞች የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ለመልካም አሥተዳደር መስፈን መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአኗኗር ዘይቤ ለስኳር በሽታ መጋለጥ ከፍ ያለ ድርሻ አለው።
Next articleሕገ ወጥ ንግድን ለመግታት ቅንጂታዊ አሠራርን ማጠናከር ይገባል።