
ደባርቅ፡ የካቲት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ አበበ ስማቸው እና አቶ ዮናስ መሐባው በሰሜን ጎንደር ዞን የደባርቅ ከተማ ኗሪ ናቸው። በደሮ እርባታ ዘርፍ ተሰማርተው በመሥራታቸው ተጠቃሚ መኾናቸውንም ይገልጻሉ።
አቶ አበበ ስማቸው እንደገለጹት ወደ እርባታ ሥራው ሲገቡ በአነስተኛ የገንዘብ ወጭ በመኖሪያ ቤታቸው መጀመራቸውን ያነሳሉ።
በአሁኑ ወቅትም ለአራት ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የእርባታ ሥራውን በፊት ከነበረው አሻሽለው እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ሌላኛው በዘርፉ የተሰማሩት አቶ ዮናስ መሐባው በበኩላቸው በእርባታ ሥራው ከግል ተጠቃሚነት አልፎ ለስድስት ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።
ሥራን ሳይንቁ በአግባቡ መሥራት እና ከሥራ ፈላጊነት ይልቅ ሥራ ፈጣሪ ወጣት መኾን እንደሚገባም አብራርተዋል።
ተጠቃሚዎቹ እንደገለጹት በደሮ እርባታ ሥራው ተጠቃሚ ቢኾኑም የመኖ እና የቦታ እጥረት ችግሮች በሥራቸው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።
ተጠቃሚዎቹ ላነሱት ጥያቄ መልስ የሰጡት የሰሜን ጎንደር ዞን እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ሸጋው ጌታቸው የቦታ ጥያቄን በሚመለከት አልሚ ሥራ ፈጣሪዎች ቦታ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ጋር በቅርበት እየሠሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
የደሮ መኖ ዋጋው እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት አቶ ሸጋው የገበያ ትስስር በመፍጠር የገበያ መረጋጋት ለመፍጠር ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስገንዝበዋል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ጊዜ የሚፈልግ በመኾኑ አማራጭ ምርቶችን አዘጋጅቶ መጠቀም የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ በደሮ ርባታ እና እንቁላል ሽያጭ ዘርፍ የሚሰማሩ አርቢዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው የባለሙያ ክትትል እና ድጋፍ በመስጠት ለማበረታታት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ነው የጠቆሙት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
