በሦስት ዓመታት ይጠናቀቃል የተባለው የዓለም ከተማ-ደጎሎ መንገድ ፕሮጀክት የት ደረሰ?

8


ባሕር ዳር: የካቲት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የዓለም ከተማ-ደጎሎ መንገድ ፕሮጀክት በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ወሎ ዞኖችን የሚያገናኝ መንገድ ነው፡፡ መንገዱ ከተጀመረ ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ ነው። አሁን ላይም ተቋርጦ ይገኛል፡፡

‎አቶ አለባቸው ኃይሌ የጃማ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከዓለም ከተማ ወደ ደጎሎ የሚወስደው መንገድ ከተጀመረ ዓመታት ቢቆጠሩም ባለመጠናቀቁ ለተሽከርካሪ አስቸጋሪ ኾኗል ብለዋል። በተለይ በክረምት ወቅት ጭቃ ስለሚኾን አምቡላንስ እንኳን ለማንቀሳቀስ አስቸጋሪ እንደኾነ ነው የገለጹት።

‎መንገዱ ሰሜን ሸዋን እና ደቡብ ወሎ ዞኖችን ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኝ በመኾኑ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ወሳኝ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ ማኅበረሰቡ በራሱ ጥረት ለመጠገን ቢሞከርም ችግሩ አልተፈታም ነው ያሉት። የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራውም ጠይቀዋል።

‎የጃማ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ለወጠኝ ጸጋው የዓለም ከተማ-ደጎሎ መንገድ ከተጀመረ ዘጠኝ ዓመታትን አስቆጥሯል ይላሉ፡፡ በጃማ ወረዳ መንገዱን የመቁረጥ፣ የመጥረግ እና የተወሰኑ የሙሌት ሥራ እንደተጀመረ በመቋረጡ መንገዱን አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል፡፡

ይህ መንገድ በጃማ ወረዳ ብቻ ለሰባት ቀበሌዎች አገልግሎት የሚሰጥ ሲኾን በተለይ ተቆርጠው ሙሌት ሳይሞሉ የቀሩ ቦታዎች በክረምት ትልቅ ፈተና እንደኾኑ ነው የገለጹት።

‎እንደወረዳ በተደጋጋሚ መንገዱ እንዲሠራ እየተጠየቀ ቢኾንም የሚሰጠው ምላሽ ከጸጥታው ችግር ጋር ስለሚያያዝ የተቋራጩ ተመልሶ ለመግባት ፍላጎት አለመኖሩንም ተናግረዋል። መንገዱ ትልቅ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው መንገድ በመኾኑ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት አለበት ነው ያሉት፡፡

‎መንገዱን ለመገንባት ውል የወሰደው የገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ኢንጅነሪንግ ዘርፍ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ሄኖክ መብራቴ የዓለም ከተማ-ደጎሎ መንገድ ውል ተወስዶ በሚያዚያ 2009 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

መንገዱ 85 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲኾን በሦሥት ዓመት ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ ውል መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

‎በአካባቢው በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ድርጅቱ ንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰበት እና ሁለት ጊዜ ሥራው መቋረጡን ገልጸዋል፡፡ በኋላም ተመልሰው ወደሥራ ገብተናል ያሉት ሥራ አሥኪያጁ ተጨማሪ የዲዛይን ሥራዎች፣ የካሳ ክፍያ ችግሮች ስለነበሩ ውሉ እስከ 2016ዓ.ም ተራዝሟል ብለዋል፡፡

‎ፕሮጀክቱ እስከተቋረጠበት ነሐሴ/2015ዓ.ም በተሠሩ ሥራዎች የአሥፋልት ንጣፍ ሥራም እንደተሠራ ገልጸዋል፡፡ የተወሰነ ያልተሠራ መንገድ ቢኖርም በአብዛኛው የቀረው የአስፋልት ንጣፍ ሥራ ነው ብለዋል፡፡

‎በአካባቢው የጸጥታ ችግር ምክንያት ድርጅቱ ንብረት እንደወደመበት አንስተው ሥራው መቋረጡን እና የጸጥታ ችግሩ ተመልሰው ለመግባት እንዳልተቻለ አሥረድተዋል፡፡ ድርጅቱ ለደረሰበት ጉዳት የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደርን የካሳ ክፍያ መጠየቁን እና ምላሽ እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡

‎በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ረጅም ዓመት የቆየ በመኾኑ በነበረው ዋጋ ለመሥራት ስለማይቻል የዋጋ ማሻሻያ ጥያቄ እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይ ተቋራጩን ወደ ሥራው ስለመመለሱ ጠይቀናቸው ገና ውይይትን እና አሥተዳደራዊ ውሳኔን የሚጠይቅ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡

‎በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የደብረ ብርሃን እና አካባቢው ፕሮጀክት አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ንጋቱ ውድነህ የመንገድ ፕሮጀክቱ የዓለም ከተማ – ደጎሎ መንገድ 1 ነጥብ 28 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለት በ2009 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

መንገዱ በተቋራጩ የግብዓት እጥረት፣ በቂ የግንባታ ማሽነሪዎች አለመኖር፣ የሰው ኃይል በሚፈለገው ደረጃ አለመኖር እና የወሰን ማስከበር ችግሮችን በጊዜው አለመፍታት ምክንያት እንደተጓተተ አብራርተዋል፡፡ በኋላም በአካባቢው የነበረው የጸጥታ ችግር በነሐሴ 2015 ዓ.ም ተቋርጧል ነው ያሉት፡፡

‎ፕሮጀክቱ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ 59 በመቶ ደርሷል ብለዋል፡፡ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል የመንገድ ቆረጣ፣ ሙሌት እና ከዓለም ከተማ እስከ ሚዳ ባለው መንገድ የ22 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ንጣፍ ሥራዎች እንደተሠሩ ነው የተናገሩት፡፡

‎ተቋራጩ በጸጥታው ችግር ምክንያት የንብረት ውድመት ስላጋጠመው 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ይከፈለኝ ጥያቄ ማቅረቡንም ጠቁመዋል፡፡ ተቋራጩ የሥራ ውሉ እንዲቋረጥ እየጠየቀ ነው፤ ነገር ግን ለመንገዱ መቋረጥ ዋናው ምክንያት የጸጥታ ችግሩ በመኾኑ ሰላም ሲኾን ውሉ ያልተቋረጠ በመኾኑ ተቋራጩ ገብቶ እንዲሠራ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጥቁር ሕዝቦች የማንቂያ ደወል ኢትዮጵያ!
Next articleበደሮ እርባታ ተሰማርተው እየሠሩ ለሚገኙ ተጠቃሚዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየተሠራ ነው።