
ባሕር ዳር፡ የካቲት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ “በሴቶች ተሳትፎ የጸናች እና የበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልዕክት ክልላዊ የሴቶች የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
የኢፌዴሪ ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ድኤታ እና የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ሥራ አሥፈጻሚ ሂክማ ከይሬዲን ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ የሴቶች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ላይ በተሠራ ሥራ ውጤት ማምጣት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ውጤት የሴቶች ክንፍ ምቹ የትግል መድረኮችን በመፍጠር የሠሯቸው ሥራዎች ታሪካዊ ለውጥ እንዲመጣ ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡
ዛሬ እየተደረገ ያለው ውይይትም በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፤ በማኅበራዊ እና በውጭ ግንኙነት መስኮች የተመዘገቡ አስደናቂ ውጤቶችን በማንሳት ለቀጣይ ተልዕኮዎች ግልጽነት ለመፍጠር ያለመ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ በሚደረገው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሴቶች በመምረጥ፣ በመመረጥ፣ በመታዘብ እና በድህረ ምርጫ ውጤትን በጸጋ በመቀበል ላይ ሚናቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸውም ነው ያስገነዘቡት።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኢሌኒ ዓባይ ሴቶችን ያላሳተፈ ሀገር ዘላቂ ልማት እና ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚቸግረው ነው የተናገሩት።
ሴቶች በፖለቲካዊ፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት ከተሳተፉ የልማት እና ሰላም ግንባታ ይፋጠናል፤ ዘላቂም ይኾናል ሲሉ አብራርተዋል። ሴቶች ሲበረቱ ትውልድ እንደሚገነባ፤ ማኅበረሰብ እንደሚጸና እና ሀገር እንደምትጸናም አንስተዋል። ኢትዮጵያም በታሪኳ ብዙ አስደናቂ የሴቶች አበርክቶ እንዳሏት ነው የገለጹት፡፡
በኢትዮጵያ ሴቶች በቁጥር ከኅብረተሰቡ 50 በመቶ እና በላይ እንደሚሸፍኑ የተናገሩት ኀላፊዋ በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ሴቶች በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የምርጫ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ሴቶች እስከዛሬ በሀገር ግንባታ ላይ የነበራቸውን ሁለንተናዊ አበርክቶ በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በተግባር እንዲያሳዩም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
