ምርጫ በማስተጓጎል ኢ-ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ለመፍጠር የሚፍጨረጨሩትን መታገል ይገባል።

5

 

ወልድያ: የካቲት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የምርጫ ማኒፌስቶ እና ምልክቱን ለአባላቱ እና ለደጋፊዎቹ አስተዋውቋል።

ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በወልድያ ከተማ የጁ ባሕል ማዕከል ለተሰባሰቡ አባላት እና ደጋፊዎቹ ነው ያስተዋወቀው።

የምርጫ ምልክቱ የስንዴ ነዶ መኾኑን የገለጹት የሰሜን ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ከድር ሙስጠፋ ትርጉሙም ልማትን፣ አንድነትን፣ ትብብርን፣ ኅብረት እና መደመር ያማለክታል ነው ያሉት።

ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለዴሞክራሲያዊ አሥተዳደር መሰረት ነው፤ ከጫካ ሥነ ልቦና ጋር ይቃረናል። በመኾኑም ይህን ምርጫ በማስተጓጎል ኢ-ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ለመፍጠር የሚፍጨረጨሩትን በጋራ በመታገል በስኬት እና በአሸናፊነት እንዲጠናቀቅ አባላቱ እና ደጋፊዎቹ እንዲሠሩ አሳስበዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር ብልጽግና ፓርቲ መደማመጥ እና ይቅርታን መርሕ አድርጎ ኢትዮጵያውያንን ደምሮ ሀገርን ከፍ የማድረግ ርዕይ አንግቦ እየሠራ ነው ያሉት።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ኢትዮጵያ በብልጽግና ጉዞ ላይ ኾና የምታካሂደው ነው ብለዋል።

ፓርቲው የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እና የዓለም ተምሳሌት ሀገር የማድረግ ዝርዝር ርዕዮችን ይዞ እየሠራ ነው ብለዋል።

የፓርቲውን ጅምር ተግባራት እና ርዕይ በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች ላሉ ለመራጩ ሕዝብ በመስተዋወቅ ረገድ አባላቱ እና ደጋፊዎቹ በትጋት አንዲሠሩ አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በድምቀት ለማክበር ዝግጅቱ ተጠናቅቋል” የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ.ር)
Next articleሴቶችን ያላሳተፈ ሀገር ዘላቂ ልማት እና ሰላምን ለማረጋገጥ ይቸግረዋል።