
ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተራዘመ ምጥ እና ያለ ዕድሜ ጋብቻ የፊስቱላ አደጋን እየጨመሩ ይገኛሉ፡፡
በ15 ዓመት ዕድሜ ትዳር እንደጀመረች ለአሚኮ የተናገራቸው ታካሚ በምትወልድበት ወቅት በተሠራ የቀዶ ጥገና ሥራ (የስቲች) ምክንያት የፊስቱላ ሕመምተኛ መኾኗን ተናግራለች፡፡ ከሕመሙ በኋላ ከትዳር አጋሯ ጋር መለያየት እንደተፈጠረ እና ብቻዋን እንደምትኖርም ገልጻለች፡፡
ከዚህ በፊት በሀምሊን የፊስቱላ ባሕር ዳር ማዕከል ቀዶ ጥገና እንደተደረገላት ያነሳችው ታማሚዋ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ እንዳልተፈወሰች ገልጻለች። ለተሻለ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ በመጠባበቅ ላይ እንዳለችም ነግራናለች፡፡
የፊስቱላ ሕመምተኛ መኾኗ የልጅነት ሕልሟ ላይ እንቅፋት እንደኾነባትም ገልጻለች። አሁን በሚደረግላት የሕክምና ክትትል በሙሉ ጤንነት ወደ ማኅበረሰቡ በመቀላቀል ሕይወቷን ለመምራት ተስፋ እንዳላት ገልጻለች፡፡
ሌላዋ ታካሚ ደግሞ በተራዘመ ምጥ ምክንያት ሁለት ልጆቿን ካጣች በኋላ በፊስቱላ በሽታ መጠቃቷን ተናግራለች፡፡
በአሁኑ ጊዜ በማዕከሉ የቀዶ ጥገና ሕክምና ተደርጎላት እያገገመች መኾኗንም ገልጻለች፡፡ በቀጣይ ከሕክምና በኋላ ወደ ማኅበረሰቡ ስትመለስ ሌሎች እናቶች ወደ ሕክምና በመሄድ አገልግሎት እንዲያገኙ የግንዛቤ ሥራ ለመሥራት ቁርጠኛ መኾኗንም ጠቁማለች፡፡
በጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የማሕጸን እና ጽንስ ስፔሻሊስት ዶክተር በላይነው ቀለብ ፊስቱላ በመውለጃ አካል፣ በሽንት ፍኛ ወይም በሰገራ መጠቀሚያ መካከል የሚፈጠር ያልተፈለገ መሰንጠቅ ነው ብለዋል።
በአብዛኛው በተራዘመ ምጥ፣ በያለዕድሜ ጋብቻ፣ በምግብ እጥረት እና በተገቢ ያልኾነ የሕክምና አገልግሎት ምክንያት እንደሚከሰት ገልጸዋል፡፡ የፊስቱላ ምልክቱም የማይቆጣጠሩት የሽንት እና የሰገራ መፍሰስ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
የፊስቱላ ጉዳት አካላዊ ብቻ ሳይኾን ከፍተኛ የሥነ ልቦና ችግርም ያስከትላል፤ ብዙ ታካሚዎች ከማኅበረሰብ መገለል፣ ከትዳር መፍታት እና የኢኮኖሚ ተጽኖ ይገጥማቸዋል ነው ያሉት፡፡
ፊስቱላ ከባድ ቢኾንም መከላከል የሚቻል እና ሕክምና ያለው ሕመም ነው። ቀድሞ በመከላከል፣ በጊዜው ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ እና ድጋፍ በመስጠት የብዙ ሴቶችን ሕይወት ከመበላሸት ማዳን እንደሚቻልም አስረድተዋል።
✍️ ፊስቱላን የመከላከያ ዋና ዋና መንገዶች፦
👉ያለዕድሜ ጋብቻን ማስቀረት
👉 የሴት ልጅ ግርዛትን ማስወገድ
👉የአመጋገብ ሁኔታን ማሻሻል
👉 ሴቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ማበረታታት
👉የተራዘመ ምጥ እንዳይፈጠር ግንዛቤ መፍጠር እና
አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር የማዋለጃ መሳሪያዎችን እና ያልተፈለገ ቀዶ ሕክምና ከማድረግ መቆጠብ እንጀኾኑ ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገር ችግሩ ከተከሰተ ከሦሥት ወር በኋላ ወደ ሕክምና ተቋም በመግባት ሕክምና ማግኘት ይቻላል ነው ያሉት።
ፊስቱላን ማከም የአንዲት ሴትን አካል ማዳን ብቻ አይደለም፤ የአዕምሮ ጤንነቷን፣ የቤተሰብ ሕይወቷን እና የማኅበረሰብ ተሳትፎዋን መመለስ ነው ይላሉ።
የባሕር ዳር ፊስቱላ ማዕከል የዋርድ ኀላፊ እና የስነ ልቦና ባለሙያ ሲስተር አያልነሽ አስረሴ የፊስቱላ ተጠቂዎች ከ70 በመቶ በላይ ከባድ የሥነ ልቦና ችግር እንደሚያጋጥማቸው ተናግረዋል።
እናቶች ችግሩ ሲከሰትባቸው ከፍተኛ ድባቴ፣ ራስን መጥላት፣ ተስፋ መቁረጥ እና ራስን እስከማጥፋት ድረስ የሚደርስ የሥነ ልቦና ጫና ይፈጠርባቸዋል ብለዋል።
ይህም ትዳር መፍታት እና ከማኅበረሰብ መለየትን ያስከትላል ነው ያሉት፡፡ የፊስቱላ ሕክምና ታካሚዎች ወደ ማዕከሉ ከሚገቡበት ግቢ ጀምሮ ተንከባክቦ ከመያዝ ይጀምራል ይላሉ።
አገልግሎቱ በቀዶ ሕክምና ብቻ አይወሰንም፤ የፊዚዮትራፒ፣ የሥነ ልቦና ምክር እና መድኃኒት ድጋፍም ይሰጣል ነው ያሉት።
በማዕከሉ በሚቆዩበት ጊዜ ፊደል እና ቁጥር መማር፣ ስለ መብቶቻቸው ግንዛቤ ማግኘት እና የሙያ ሥልጠናም እንደሚሰጣቸው አስገንዝበዋል።
ሲወጡም ከአጋር ድርጅቶ ጋር በመተባበር እራሳቸውን የሚያቋቋሙበት ድጋፍ ይደረግላቸዋል ነው ያሉት፡፡
ይህም ከማዕከሉ ከወጡ በኋላ ራሳቸውን ችለው እንዲኖሩ እንደሚረዳቸው ጠቁመዋል።
ተፈውሰው ወደ ማኅበረሰቡ የተመለሱ ሴቶች ጋር የልምድ ልውውጥ ይደረጋል፤ ይህም ተስፋቸው እንዲጠናከር እና በቀላሉ እንዲቀላቀሉ ያግዛቸዋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
