የቀይ ባሕር ነጋዴው – ትዝታ

18

 

ባሕር ዳር: የካቲት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ1935 ዓ.ም በባሕርዳር አቅራቢያ ነው የተወለዱት፡፡ ገና በልጅነታቸው ነጋዴነትን የሕይወታቸው መስመር አደረጉ፡፡

ከአዲስ አበባ – አሥመራ ተመላልሰው ነግደዋል፡፡ ዝሃ፣ ሳሙና፣ ኦሞ፣ ጨው እና ላምባ ዋና የንግድ ሸቀጦቻቸው ነበሩ፡፡ በፊት በበቅሎ፣ የዓባይ ድልድይ ከተሠራ በኋላም በመኪና ነግደዋል፡፡ ከኢትዮጵያም የግብርና ምርቶችን ጭነው በመውሰድ ያቀርቡ ነበር ሀጂ ተዘራ አበበ፡፡

የዛኔው የንግድ ግንኙነት በአሥመራ የኾነበት ምክንያት ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል እና የወደቦች (አሰብ እና ምጽዋ) መገኛ ስለነበረች መኾኑን አስታውሰዋል፡፡ በቀይ ባሕር አቋርጦ በወደብ የሚራገፈውን ወደ መሃል ሀገር፣ ከመሃል ሀገር የያዚትን ደግሞ ወደ ወደብ ይወስዱ ነበር። ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ነጋዴዎች የንግድ መመላለሻ መሰመር እንደነበር ያነሳሉ።

ኢትዮጵያ ወደብ በነበራት ጊዜ የሸቀጦች ዋጋ ርካሽ እንደነበር አንስተዋል። ዛሬ ላይ ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩም ለሸቀጦች ዋጋ መናር ዋናው ምክንያት የወደብ ኪራይ እንደኾም ገልጸዋል።

በእነ ሀጂ ተዘራ ዘመን ኢትዮጵያ የባሕር በር እና ወደብ ነበራት፡፡ ወደቡም፣ ንግዱም፣ ላኪውም፣ ተቀባዩም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ መተማመን እንጂ መካካድ የለም፡፡ ከወደብ ያለው ነጋዴ ለመሀል ሀገሩ ይልክለታል፤ ገንዘቡን ሲመቻቸው ይቀባበላሉ፡፡ የአንድ ሀገር ሰዎች ስለኾኑ የዋጋ መብዛት እና የመተማመን ጉዳይም አያሰጋቸውም ነበር፡፡

የወጪ እና ገቢ ንግዱን በኪራይ ወደብ የሚፈጽም ሀገር የዶላር ወጪው ብቻ ሳይኾን የሀገር ወታደራዊ ምስጢር እና ደኅንነቱም አደጋ ውስጥ ይገባል፡፡ ባለወደብ ሀገራት ወታደራዊ ምስጢርህን እና አቅምህን ያውቃሉ፡፡ በተኳረፍክ እና በተጋጨህ ጊዜም አቅምህ የሚታወቅ ነው ይላሉ ሀጂ ተዘራ፡፡

በመኾኑም ኢትዮጵያውያን የባሕር በርን አስፈላጊነት በወደብ ብቻ አሳንሰው ማየት እንደማይገባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡

ኀያላን ሀገራት እኛ እየለመንን እንድንኖር እንጂ ራሳችን ችለን እንድንኖር ፍላጎቱ የላቸውም ያሉት ሀጂ ተዘራ ያንን ፍላጎታቸውን የሚታገል መንግሥትን ለማዳከም የማይሄዱበት ርቀት እንደሌለ ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያን ከኀያላን ሀገራት ጫና ለማላቀቅ የሞከሩ ሥርዓቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ መንግሥታቱን ከሕዝብ በማቃቃር አንድነቷን ማዳከም እና ልማቷን ማደናቀፍ የተለመደ ሥራቸው መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

አሁንም መንግሥት ኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤት ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት መደገፍ አማራጭ የሌለው መኾኑን አንስተዋል፡፡

ግብጽ ጸረ – ኢትዮጵያ ሴራዎችን ከመሸረብ እና ከመደገፍ እንደማትመለስም ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብም በሁሉም ረገድ የሀገሩን ጥቅም ማስጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት ወሳኙን የባሕር በር ለማግኘት ለሚጥረው መንግሥት ሕዝቡ መተባበር እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡

እኛ መንግሥታት ካለፉ በኋላ ማመስገን እና መጸጸት ለምዶብናል ያሉት ሀጂ ተዘራ ኢትዮጵያን የማልማት እና ወደ ቀደመ ክብሯ የመመለስ ጥረትን አሁን ላይ መደገፍ እና የታሪኩ ተሳታፊ መኾን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ለጊዜው የሚመጥን እውቀት እና ብልህነትም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በጎንደር ከተማ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
Next articleፊስቱላን ማከም የአንዲት ሴትን አካል ማዳን ብቻ አይደለም፡፡