
ጎንደር: የካቲት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከፍቷል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ጎንደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለው እዘዘው በአማራ ክልል ደሴ እና ባሕር ዳር ከተሞች ብቻ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በማስፋት የፓስፖርት ምዝገባ እና አገልግሎት በጎንደር፣ በደብረ ብርሃን እና ወልድያ ከተሞች አገልግሎት እየሰጠ መኾኑን ገልጸዋል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ጎንደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮ 400 ለሚኾኑ ዜጎች ፖስፖርት መስጠት መቻሉንም አስረድተዋል። ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በዓመት እስከ 90 ሺህ ለሚኾኑ ዜጎች አገልግሎት መስጠት እንደሚችልም ተገልጿል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ጎንደር ላይ ሥራ መጀመሩ የማኅበረሰቡን ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መኾኑን አመላክተዋል።
ጎንደር የበርካቶች መዳረሻ እና ማዕከል መኾኗን ያነሱት ምክትል ከንቲባዋ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት ከተማ አሥተዳደሩ ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ጋር በጋራ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ፓስፖርት ሲወስዱ ያገኘናቸው ተገልጋዮችም ከዚህ ቀደም ፖስፖርት ለማግኘት ያጋጥማቸው የነበረውን እንግልት፣ ወጪ እና ጊዜ ያስቀረ መኾኑን አንስተዋል።
ተገልጋዮች አስፈላጊ መረጃዎችን ይዞ በመቅረብ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉም የጎንደር ኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
