
ገንዳውኃ: የካቲት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የገንዳውኃ ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ እና መደበኛ የትራፊክ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከባጃጅ አሽከርካሪዎች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ካላስፈላጊ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በመራቅ በከተማው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል። በሚደረገው ሕግ የማስከበር ተግባር ከመንግሥት ጎን መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ለሰላም እና ለልማት እንደሚተባበሩም ተናግረዋል። በማደያዎች አካባቢ የሚሠራው ሕገወጥ አሠራር እንዲቆምላቸውም ጠይቀዋል።
የገንዳውኃ ከተማ አሥተዳደር መንገድ እና ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስፋው ከተማ እንደገለጹት ሁሉም አሽከርካሪዎች ለሰላም እና ለለውጥ አርዓያ በመኾን ለጋራ ዕድገት መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
አሽከርካሪዎች በሰዓት ዕላፊ ከማሽከርከር በመቆጠብ ራሳቸውን እና ሀገርን ከአደጋ መጠበቅ እንደሚገባቸው አስረድተዋል።
የገንዳውኃ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ኀይሌ ብርሃኑ ሰላምን ለማረጋገጥ እና ማኅበረሰቡን በቅንነት ለማገልገል እየተሠራ ነው ብለዋል።
ሕግ እና ሥርዓትን በመጠበቅ ከተለያዩ የወንጀል ነክ ድርጊቶች በመቆጠብ እና መልካም ስብዕና የተላበሰ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
