
ባሕር ዳር: የካቲት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ)በባሕርዳር ዙሪያ እና በሰሜን ሜጫ ወረዳዎች በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል።
የሰላም አማራጭን የተቀበሉት ታጣቂዎች በመርዓዊ ከተማ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የሰላም አማራጭን ከተቀበሉት መካከል በታጣቂ ቡድኑ አደረጃጀት ከፍተኛ ኀላፊነት የነበራቸው ይገኙበታል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን ወደ ሕዝባችሁ መቀላቀላችሁ እና የሰላምን አማራጭ በመቀበላችሁ ለሕዝቡ ትልቅ እፎይታን ይሰጣል ብለዋል።
መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት የተሃድሶ ሥልጠና በመውሰድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲወጡም አስገንዝበዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ኃላፊ ማስተዋል አሰሙ የሰላምን ዋጋ ተረድታችሁ ሰላምን ስትቀበሉ ሕዝባችሁን ለመካስ ያላችሁን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎችም በተሳሳተ መንገድ የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርገን ቆይተናል ነው ያሉት። ከሻቢያ እና ሕወሃት ጋር አብሮ መሥራት ሕዝባችንን ይባስ እንደበደለው ስለተረዳን ሰላምን መርጠናል ብለዋል።
ከሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ሕዝብን ለመካስ ዝግጁ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
