
ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደባርቅ-ሊማሊሞ- ዛሪማ መንገድ በኢትዮጵያ ውስጥ አስቸጋሪ ከሚባሉ መንገዶች መካከል ይጠቀሳል፡፡ መንገዱ ከተገነባ ከ80 ዓመታት በላይ ኾነውታል።
የመንገዱ አስቸጋሪነት፣ ጠመዝማዛነት እና ረጅም አገልግሎት ከመስጠቱ አንጻር የፈራረሰ መኾኑ ለአሽከርካሪዎች እና ለመንገደኞች ፈተና ኾኖ ቆይቷል። መንገዱ ጥገና እንዲደረግለት ወይም ተለዋጭ መንገድ እንዲሠራለት በማኅበረሰቡ በኩል በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡
በዚህ መነሻነትም በ2011 ዓ.ም ከ2 ነጥብ 1ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት የተለዋጭ መንገድ ግንባታ መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡
መንገዱ 68 ነጥብ 62 ኪሎ ሜትር ይረዝማል። በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ በመገንባት በአራት ዓመታት ለማጠናቀቅ ውል ተይዞለትም ነበር፡፡
ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ የተለዋጭ መንገዱ አለመሠራቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በደባርቅ ወረዳ የላይ ቦዛ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጀጃው ብርሃኑ መንገዱ ከ30 ዓመታት በላይ ማኅበረሰቡ ሲጠይቀው የኖረ ጥያቄ መኾኑን ተናግረዋል። ጥያቄው ምላሽ አግኝቶ ግንባታው ቢጀመርም ሳይሠራ ተቋርጦ ቀርቷል ብለዋል።
ከዛሬ ነገ ግንባታው ይቀጥላል የሚል ተስፋ ቢኖራቸውም እስከ ዛሬ ድረስ እንደተቋረጠ መቅረቱን ገልጸዋል። ወላድ እናቶች እና አቅመ ደካሞች ሕክምና ለመድረስ እየተቸገሩ መኾናቸውንም አንስተዋል።
ማኅበረሰቡ ያመረተውን ምርት በሚፈለገው ልክ ለገበያ ማቅረብ እንዳልተቻለም ተናግረዋል። በዚህም የአካባቢው ማኅበረሰብ ቅሬታ ውስጥ መግባቱን ነው የሚናገሩት።
የሰሜን ጎንደር ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ ተወካይ ጥጋቡ በቀለ የመንገዱ ግንባታ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ መቋረጡን አስታውቀዋል። ግንባታው እንዲቀጥል በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር በደብዳቤ ቢያቀርቡም ተጨባጭ ምላሽ ሊሰጥ እንዳልቻለ ተናግረዋል። ይህም ከፍተኛ የመልካም አሥተዳደር ችግር የፈጠረ በመኾኑ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የጎንደር ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዳንኤል ንጉሤ የተለዋጭ መንገዱ ግንባታ ተጀምሮ 24 በመቶ ደርሶ እንደነበር ገልጸዋል። ነገር ግን በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት መቋረጡን ተናግረዋል።
አማካሪውም ሥራ ተቋራጩም የውጭ ድርጅቶች በመኾናቸው በተፈጠረው ችግር ምክንያት ሥራውን አቋርጠው ከሀገር ወጥተዋል ነው ያሉት።
ግንባታውን በሌላ ሥራ ተቋራጭ ለማስቀጠል አማካሪ ድርጅቱንም ማግኘት ባለመቻሉ በአዲስ ለማስቀጠል መዘግየቱን ተናግረዋል። በዚሁ ጉዳይም አሥተዳደሩ ከተቋራጩ ጋር ለረጅም ጊዜ በክስ ክርክር ላይ መቆየቱንም ጠቁመዋል።
የመንገዱን ቀሪ ሥራ በሌላ ሥራ ተቋራጭ ለማስጨረስ በተያዘው በጀት ዓመት የጨረታ ሰነድ ተዘጋጅቶ በጀት ተይዞለታል ብለዋል። ከሌሎች ከተቋረጡ ፕሮጀክቶች ጋር ውሳኔ ሲሰጠው ወደ ሥራ እንደሚገባም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
