
ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለሀገር ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ እድገት መንገድ ወሳኝ ሚና አለው።
በኢትዮጵያ እየተሠሩ ካሉ ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል ከዓለም ባንክ በተገኘ ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ እየተገነባ የሚገኘው የቡሬ-ነቀምት አስፋልት መንገድ አንዱ ነው።
አማራ ክልልን ከኦሮሚያ ክልል የሚያገናኘው የአብሮነት ማጠንከሪያው ይህ 259 ኪሎ ሜትር መንገድ ያለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ጠቀሜታ እና የትራፊክ ፍሰት ከፍተኛ ነው፡፡
ለአሠራር አመቺነት ሲባልም መንገዱ በሦሥት ተቋራጮች ተከፋፍሎ የግንባታ ሥራው እየተከናወነ ይገኛል።
ከነዚህ መካከል 84 ነጥብ 55 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው የቡሬ- አጋምሳ ሎት ሦሥት የመንገድ ፕሮጀክት አንዱ ክፍል ነው። 1ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለት ነው እየተሠራ የሚገኘው።
መንገዱ በ2012 ዓ.ም ተጀምሮ በሦሥት ዓመታት ተሠርቶ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢኾንም ከአምስት ዓመታት በላይ ተቆጥረውም አልተጠናቀቀም።
ይህን ተከትሎም አሚኮ ዲጅታል ሚዲያ የመንገድ ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ያለበትን ሁኔታ ከአካባቢው ነዋሪ እና ፕሮጀክቱን ከሚከታተለው የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የነቀምቴ አካባቢ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ጋር ቆይታ አድርጓል።
በንግድ ሥራ ዘርፍ ተሠማርተው ለረጅም ዓመታት ከቡሬ ነቀምት በተደጋጋሚ ለሥራ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ሃሳብ ሰጫችን መንገዱ በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ብሔር ብሔረሰቦችን ለዘመናት ሲያገናኝ መቆየቱን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል አስቸጋሪ የጠጠር መንገድ በመኾኑ የአካባቢውን ነዋሪዎች እና በመንገዱ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ አሽከርካሪዎችን ለእንግልት ሲዳርግ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በርካታ የነቀምት ነዋሪዎች ከቅርበት አንጻር ለሕክምና ሪፈር የሚባሉት ወደ ቡሬ ጠቅላላ ሆስፒታል ስለነበር ታካሚዎች በተለይም ደግሞ ወላድ እናቶች ይንገላቱ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
አካባቢው ሰፊ የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች እንዲሁም እጣን የሚመረትበት ቢኾንም የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚሰጥ የመንገድ ችግር ስለነበር የአካባቢው አርሶ አደሮች እና በኢንቨስትመንት የተሠማሩ ድርጅቶች ምርት አምርተው ወደ ገበያ ለማቅረብ ይቸገሩ ነበር ብለዋል።
የታላቁ ዓባይ ወንዝ በረሃማ አካባቢ የጎብኝዎች መዳረሻ የነበረ ሳቢ ቦታም የቱሪዝም መዳረሻ እንዳይኾን ተጽዕኖ ፈጥሯል ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን ችግሮች በመረዳት የአስፋልት መንገድ ሥራ ሲያስጀምር የሁለቱ ሕዝቦች ደስታ ከፍተኛ ነበር ነው ያሉት።
መንገዱ እየተቆራረጠ ሢሠራ የቆዬ ቢኾንም አሁን ላይ የአስፋልት ግንባታ ሥራው መቀጠሉን ነው የጠቀሱት። መንገዱ አስቸጋሪ በመኾኑ እና የአስፋልት ግንባታ ሥራው በተቀመጠለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ግን የአካባቢው ነዋሪዎች ለእንግልት ተዳርገዋል ብለዋል። የአስፋልት መንገድ ሥራው ተጠናቅቆ ለሁለቱ ክልል ሕዝቦች አገልግሎት እንዲሰጥም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የነቀምቴ አካባቢ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ኢንጂነር ዲንቂሳ ነሜ ደግሞ የቡሬ አጋምሳ ሎት ሦሥት መንገድ የተቋራጭ ለውጥ በመደረጉ እና በጸጥታ ሁኔታው ምክንያት በመጡ ችግሮች በተቀመጠለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ አድርጓል ብለዋል።
መንገድ ፕሮጀክቱ ሲጀመር የነበረው ሥራ ተቋራጭ ጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ የነበረው ቢኾንም በአካባቢው በነበረ የጸጥታ ችግር ምክንያት መቀጠል ባለመቻሉ ውሉ ተቋርጦ ከ2016 ዓ.ም ወዲህ ሌላ ተቋራጭ ውል ይዞ እየሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል። የመንገድ ሥራው ተቋርጦ ቆይቶ በ2017 ዓ.ም ዳግም ወደ ሥራ መግባቱንም አስታውሰዋል።
ከ2017 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ በሙሉ አቅም መንገዱ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት። አሁን ላይ በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኘው ከቡሬ እስከ ዓባይ ወንዝ ድልድይ ያለው 58 ኪሎ ሜትር መንገድ ከ50 ኪሎ ሜትር በላዩ ኪሎ ሜትር አብዛኛው የመንገድ ሥራ ተጠናቋል ብለዋል። ቡሬ ከተማ እና የዓባይ ድልድይ አካባቢ የሚቀሩ ውስን ሥራዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።
መንገዱ ትልቅ የመንገድ ኮሪደር ነው ያሉት ኢንጅነሩ አጠቃላይ የሎት ሦሥት መንገድ ፕሮጀክት 65 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን ነው የገለጹት።
መንገዱን በመጭው ታኅሳስ ወር 2019 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
