በአማራ ክልል ከ1 ሺህ 300 በላይ ትምህርት ቤቶች የምገባ መርሐ ግብር ጀምረዋል።

2

 

ጎንደር: የካቲት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በጎንደር ቀጣና ከተውጣጡ የዞን እና የወረዳ የትምህርት አካላት ጋር የስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸሙን በጎንደር ከተማ እየገመገመ ነው።

የትምህርት ዘርፉ ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ ፈተናዎች የገጠሙት መኾኑን በዕለቱ የተናገሩት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ ናቸው።

ይሁንና የደረሰውን የትምህርት ስብራት ለማከም ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እየተሠራ መኾኑን ገለጸዋል።
በክልሉ 11 ሺህ ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲኾን ከዚህ ውስጥ ከ83 በመቶ በላይ የሚኾኑት ወደ ሥራ ገብተዋል ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው።

ተማሪዎችን ለማብቃት እና ለፈተና ለማዘጋጀት የመምህራን ብቃት ወሳኝ ነው፤ መምህራንን የማብቃት ተግባር ላይ ትምህርት ቢሮው በትኩረት እየሠራ ነውም ብለዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ለ9 ሺህ 710 የትምህርት ተቋማት ማሻሻያ መሠራቱንም ጠቅሰዋል።

በክልሉ የሦስት ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እና አራት የሞዴል ትምህርት ቤቶች ግንባታዎች እየተጠናቀቁ መኾኑንም ጠቁመዋል። በቀጣይ ዓመትም ወደ ሥራ እንደሚገቡ አስረድተዋል ።
በክልሉ በከተማ እና በገጠር አካባቢዎች 1 ሺህ 335 ትምህርት ቤቶች ምገባ መጀመራቸውንም ትምህርት ቢሮው አስታውቋል።
ለዚህም በክልሉ መንግሥት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ እየተሠራ ነው ብለዋል ምክትል ኀላፊው።

በጎንደር ከተማም በትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ላይ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ናቸው።

የምክክሩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የገጠመውን የሰላም እጦት ተቋቁሞ የተሻለ መማር ማስተማር ለመፍጠር እንደየ አካባቢያቸው ሁኔታ አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን አንስተዋል።

ዘጋቢ፦ ዳንኤል ወርቄ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰላምን ለማስከበር በሥነ ልቦና እና በአቅም መዘጋጀት ያስፈልጋል።
Next articleሴቶች ተጠቃሚ እንዲኾኑ ብልጽግና ፓርቲ እየሠራ ነው።