ሙያን ለባለቤቱ ብንተውለትስ?

8

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት15/2018ዓ.ም (አሚኮ) ዘመን ዘመንን እየወለደ በሄደ ቁጥር የሰው ልጆች የፈጠራ ጥበብም አብሮ እያደገ መሄዱ አይቀሬ ነገር ነው።

ከሰው ልጅ የፈጠራ ጥበቦች መካከል አንዱ መረጃን ለመለዋወጥ የተፈጠረው የማኅበራዊ ሚዲያ ጥበብ ይጠቀሳል። ይህ ጥበብ አሁን ላይ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን እርስ በርስ የሚያገናኝ ትልቅ ምህዳር ኾኗል።

ብዙ ሰው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ያጋራል፤ ሌሎች ያጋሩትንም ይመለከታል። እኔም ከእነዛ ሰዎች መካከል አንዷ ነኝና የሚጋሩ መረጃዎችን እና መረጃ አጋሪዎችን ለመታዘብ ሩቅ አይደለሁም።

ቀኑ ዕለተ ሰንበት በግምት ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ነበር። ዛሬ ምን አዲስ ነገር አለ ብየ ለመረጃ ቅኝት የእጅ ስልኬን በማንሳት ወደ ፌስ ቡክ ገጽ ጎራ አልኩ። ቀጠልኩና የመረጃዎችን ርእስ አለፍ ሲልም ፎቶ እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ቃኘሁ።

በዚህ መካከል ነው እንግዲህ ለዛሬው ትዝብቴ መነሻ የኾነ በ100 ሺህ የሚቆጠሩ አባላት ያሉበት ቡድን ላይ የተጋራ መረጃ ቀልቤን ያዝ አድርጎ የሀሳብ ትርምስ ውስጥ የከተተኝ።

መረጃ አቅራቢው የጤና ምክረ ሃሳብ ፍለጋ ነበር መረጃውን ያጋራው። ይህን ተከትሎም ብዙዎች ይሄን አድርግ…፣ ይሄን አድርግ …እያሉ ሃሳብ እያስቀመጡ ነበር።

እኔም ልጁ ለጠየቀው ጉዳይ አጋዥ ሀሳብ ያገኘ አልመሰለኝምና ተመሳሳይ የሚመስል ሁኔታ ገጥሞኝ ስለነበር ከልምዴ ተነስቸ ሀሳቤን እንደሌሎቹ ሰዎች አጋራሁ። ከዛ ግን ድንገት ከዚህ ሁሉ ሀሳብ ሰጭ ማን ነው ለጉዳዩ ቅርብ ሙያ ያለው ብየ የምክር ሰጭዎችን ግላዊ መረጃ ማየት ጀመርኩ። የሚገርመው እንደ እኔ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌለው ሙያ ላይ የተሠማሩ ሰዎች ናቸው የመፍትሔ ሃሳብ ሰጭዎች።

ኽምም… አስባችሁታል ድርድር ውስጥ ለማይገባው የጤና ጉዳይ?

በቀጣይ የየዘርፉ ሙያዎች እጣ ፈንታ ከወዲሁ ካላረምነው ከባድ የሚኾን ይመስለኛል! ለነገ ዛሬ ላይ ማሰብ ያስፈልጋልም እላለሁ።

ወደ ጀመርኩት ትዝብቴ ልመለስ። ይህን ተከትሎም መፍትሔ ፈልጎ መረጃ ያጋራውን ሰው ጨምሮ በርካታ ሰዎች በአስተያየት መስጫ ሳጥን ላይ የሰጠሁትን ሀሳብ በማየት እንደወደዱት የሚገልጽ ምልክት ይደርሰኝ ጀመር።

በዚህ መካከል ከአንድ አስተያየት ሰጭ በውስጥ መልዕክት ደረሰኝ። በሰጠሁት ሀሳብ አመስግኖ የሕክምና ስፔሻሊስት ነሽ? የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ። እኔም ነገሩ አስገርሞች ፈገግ ብየ የሳቅ አመላካች ምስል ከኋላ አስከትየ አይ የቃላት፣ የድምጽ እና ምስል ስፔሻሊስት ነኝ አልኩት።

እሱ ግን ሙያየ ምን ሊኾን እንደሚችል መገመት አልከበደውም መሠለኝ ታዲያ እንዴት ጋዜጠኛ የሕክምና ምክረ ሀሳቦችን ይሰጣል አለኝ።

እምም…ከባድ ሰው!

እኔም ከሙያ አንጻር ሳይኾን ማንኛውም ሰው ሃሳብ እንደሚሰጠው ለመሳተፍ ያክል ራሴን ከገጠመኝ ተመሳሳይ ሁኔታ ጋር አስተሳስሬ ከጠቀመ ብየ ነው ያጋራሁ አልኩት። ግን እኮ ልክ አይደለሁም! ከንቱ ልምምድ ነውና ሙያውን ለባለቤቱ መተው ነበረብኝ!

በዚህ መካከል አንድ ጓደኛየ ያለችኝ ሃሳብ ትዝ ብሎኝ እንደሞኝ ፈገግ አልኩ። ይህ ማኅበራዊ ሚዲያ የማያደርገን የለም እኮ ጓደኛየ፤ ለጸጉርሽ፣ ለፊትሽ…እያሉ ያለሙያቸው መረጃ በሚያጋሩ ሰዎች ያልተሞከረ ነገር የለም፤ ምን አልባት በርበሬ ጭንቅላት ላይ ከመስቀል ውጭ ያለችኝ ሀሳብ።

…ብቻ ያለሙያችን ምክረ ሃሳብ ሰጭ የኾነውን ቤት ይቁጠረን።

ወጣቱ የዋዛ አይደለምና በጉዳዩ ላይ ሃሳቡ ቀጠለ። የሚገርመው እኮ የፌስቡክ የጦር ጄነራሎችም በዝተዋል አለኝ። ልክ ነው እንደ ጋዜጠኞች ባይበዛም ብየ ቀልድ መሠል ቁምነገር የተሞላበት ሃሳቤን በሳቅ ምልክት አዋዝቸ ሃሳብን በሃሳብ መለስኩለት።

ከዛም ሥራን ለሠሪው መተው ካልቻልን ከባድ ሁኔታ ላይ ነን አልኩና ሃሳቤን ገታ አደረግሁ። በአጋጣሚ ውይይት የጀመረው ወጣት ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር ካልተፈጠረ ከባድ ነው አለኝ። ሕግ እኮ አለ የአተገባበር ውስንነት እንጂ አልኩት።

ጉድ ፈላ ከተተገበረ እኮ ሁላችንም አለቀልን ሲል አገላለጹ ገርሞኝ ከልቤ ስቄ ራሴን እንድመለከት ምክንያት ኾኖ ሃሳብ ስላጋራኝ አመስግኘ ተሰነባበትን።

በዚህ መካከል የምናጋራቸው መረጃዎች፣ የምንሰጣቸው ሃሳብ እና አስተያየቶች በመሰለኝ እና በግላዊ አረዳድ ሊኾኑ እንደማይገባ ተገነዘብኩ።

ውድ አንባቢያን እናንተም የታዘብኩትን ትዝብት ለትምህርት እና እርምት ትጠቀሙበት ዘንድ አጋራዋችሁ።

ማኅበራዊ ሚዲያዎች ከአዋቂነት ይልቅ ታዋቂ ለመኾን ጥረት የሚደረግባቸው፣ ሁሉ ጋዜጠኛ፣ ሁሉ ሀኪም፣ ሁሉ መምህር፣ ሁሉ የጦር ጄኔራል …የሚኾኑበት ምህዳር ሊኾኑ አይገባም።

በጥቅሉ ሙያን ለባለቤቱ መተው ይገባል እላለሁ!

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የእኛ ሠራዊት የተግባር እንጂ የንድፈ ሃሳብ አይደለም” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
Next article“አየር ወለዶች የኢትዮጵያ ልዩ ስጦታዎች ናቸው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)