ለሀገር ዕድገት የወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መኾኑን የደባርቅ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።

7

 

ደባርቅ: የካቲት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የሥነ አዕምሮ ጤና አጠባበቅን በሚመለከት ለወጣቶች የሥልጠና መርሐ ግብርን በደባርቅ ከተማ አካሂዷል።

በሥልጠናው የተሳተፉ ወጣቶች የሥነ አዕምሮ ጤና አጠባበቅ እና የሕይዎት ክህሎት ሥልጠናዎች የወጣቶችን የነገ ሕይዎት ብሩህ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

ወጣቶች በሥራ አጥነት እና በአቻ ግፊት ምክንያት ተስፋ በመቁረጥ ወደ ሱስ እና መሰል ማኅበራዊ ችግሮች እንዳይገቡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች መሠራት አለባቸው ብለዋል።

ወጣቶች በአካል እና በሥነ ልቦና ጤናማ ኾነው ሕይዎታቸውን እንዲመሩ እና አምራች እንዲኾኑ ለማስቻል ሁሉም ባለድርሻ አካል ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ተሳታፊዎቹ ከሥልጠና ባለፈ ቋሚ የሥነ ልቦና ማማከር አገልግሎት መስጫ ማዕከል እንዲቋቋም እና አገልግሎት እንዲያገኙ ጠይቀዋል።

ሥልጠናውን የሰጡት በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ተዋልዶ እና የሥነ-አዕምሮ ጤና መምህሯ አገሬ መንግሥቴ በተለያዩ ምክንያቶች ራሳቸውን የሚያጠፉ ወጣቶች ቁጥር ቀላል እንዳልኾነ ተናግረዋል።

ይሄም ማኅበራዊ ቀውስ የሚያስከትል በመኾኑ ሥልጠናውን ለመስጠት እንዳነሳሳቸው ነው የተናገሩት።

በሥልጠናው የአዕምሮ ጤና አጠባበቅ፣ የአቻ ግፊትን መቋቋም እና ከሱስ ማገገም የሚሉ ጉዳዮች እንደተዳሰሱም ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማኅበረሰብ ዓቀፍ አገልግሎቶች ዳይሬክተር ጌታቸው ውለታው ተሳታፊዎቹ ላነሱት የቋሚ ማዕከል ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በመተባበር የወጣት ማዕከላትን ለማልማት እና ቋሚ የሥነ ልቦና ማማከር አገልግሎት መስጫ ማዕከል ለመክፈት ዩኒቨርሲቲው እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሥልጠናው በየደረጃው ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች በቀጣይነት እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሀገር መከላከያ ሠራዊት ታላላቅ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን ይፈጽማል፤ ሕዝብ ደግሞ አካባቢውን በትጋት ይጠብቃል” አቶ ደስታ ሌዳሞ
Next article👉 ውብሸት ወርቃለማሁ