ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂው ዘርፍ የፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ታዳጊዎች በማብቃት በኩል በትኩረት እየሠራ ነው።

8

 

ደባርቅ: የካቲት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በስቲም ማዕከል፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ተግባር ተኮር ሥልጠና ሲወስዱ የቆዩ ተማሪዎችን አስመርቋል።

ዩኒቨርሲው ከ60 በላይ የሚኾኑ ተማሪዎችን በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግ እና በሒሳብ ዘርፎች የማጠናከሪያ ተግባር ተኮር ትምህርት ሲሰጥ ቆይቷል።

ተሳታፊ ተማሪዎቹ ሥልጠናው በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን ትምህርት ወደ ተግባር በመለወጥ የተሻለ ሳይንሳዊ እውቀት እንዲያዳብሩ እንዳገዛቸው ገልጸዋል።

ሥልጠናውን የተሳተፉት የዘጠኝ እና አስረኛ ክፍል ተመሪዎች በመኾናቸው በቀጣይ በመሰናዶ ትምህርት ቤት ለሚመርጡት የተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ አጋዥ መኾኑንም ተናግረዋል።

በመርሐ ግብሩ የግል ተሞክሮውን እንዲያጋራ አሚኮ ያነጋገረው ተማሪ መሳፍንት አስረስ በዩኒቨርሲቲው ባገኘው ሥልጠና በመታገዝ በሀገር አቀፍ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን አጫውቶናል። ዩኒቨርሲቲው ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ውድድሩን እንዲያጠናቅቅ ምክንያት መኾኑንም ነግሮናል።

በዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሥልጠና ድጋፍ በሱ እና በጓደኞቹ ዘንድ ከፍ ያለ የፈጠራ መነቃቃት መፍጠሩን ገልጿል።

በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች ዳይሬክተር ጌታቸው ውለታው ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ በክረምት እና በበጋ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ተመሳሳይ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሥልጠናዎችን ለመስጠት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የፈጠራ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን እንዲሠሩ ሁኔታዎችን በማመቻቸት እያገዘ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማኅበረሰብ ዓቀፍ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ጋሻው ግስሙ (ዶ.ር) ዘመኑን የሚመጥን ዕውቀትን ለማዳበር እና በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመኾን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዕውቀቶች ወሳኝ ናቸው ብለዋል።

ተማሪዎች ከሥልጠናው ባገኙት ዕውቀት እና ክህሎት ሳይገደቡ ጠንክረው በመሥራት እና ተጨማሪ አቅም በመፍጠር አቅማቸውን ሊያዳብሩ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በሳይንስ እና ቴክኖሎጂው ዘርፍ የፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ታዳጊዎች በማብቃት በኩል ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮ-ዓለም አቀፍ ሳይንስ እና ትምህርት የወጣቶች ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ተከፈተ።
Next article“የሀገር መከላከያ ሠራዊት ታላላቅ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን ይፈጽማል፤ ሕዝብ ደግሞ አካባቢውን በትጋት ይጠብቃል” አቶ ደስታ ሌዳሞ