
ወልድያ፡ የካቲት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወልድያ ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰብ አገልግሎት ያከናወናቸውን ተግባራት እና ሊሠራቸው የሚገባ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ምክክር ከሰሜን ወሎ ዞን፣ ከዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና ከወልድያ ከተማ አሥተዳደር ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና የሥራ ኀላፊዎች ጋር መክሯል።
ዩኒቨርሲቲው በትምህርት፣ በግብርና፣ በጤና እና መሰል ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በሦሥቱም ክላስተሮች የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እየሰጠ መኾኑ ተገልጿል።
የትራንስፖርት ዘርፉን ማሻሻል፣ ምርጥ ዘር ብዜት፣ የእንስሳት ሕክምና እና ክትባት፣ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ፣ ሕገወጥ ስደትን መቆጣጠር፣ የነጻ ሕግ አገልግሎት፣ የሕክምና አገልግሎት፣ የወባ በሽታ መከላከል እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ዩኒቨርሲቲው ለማኅበረሰቡ አገልግሎት መስጠቱ ተመላክቷል።
ዩኒቨርሲቲው የሚሠራቸውን ተግባራት ለኅብረተሰቡ የማስተዋወቅ ጉድለት ስለነበረበት ስለሚሠራቸው ሥራዎች ግንዛቤው እንዳልነበራቸው ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።
ይህን መሰል ኅብረተሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ ተግባራት ሲከውኑ ማኅበረሰቡ እንዲያውቀው ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት እንዲዘረጋም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ጉድኝት ምክትል ኘሬዝዳንት ማርዬ በለጠ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው በ2017 በጀት ዓመት ብቻ በ25 ኘሮጀክቶች የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠቱን ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ደግሞ 25 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘላቸው 15 ኘሮጀክቶችን ዩኒቨርሲቲው አገልግሎት በሚሰጥባቸው ሦሥት ወረዳዎች ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል።
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት አበበ ግርማ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ቢደርስበትም ከመማር ማስተማር ባሻገር በምርምር እና በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዘርፍ የኅብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግር ለማቅለል ትኩረት ሰጥቶ ሢሠራ ቆይቷል ብለዋል።
ወደፊትም ኅብረተሰቡን ተደራሽ ለማድረግ በትጋት ይሠራል ነው ያሉት።
ከተሳታፊዎቹ የተነሳው ሥራዎችን ለኅብረተሰብ የማሳወቅ ጉድለት ጥያቄ ትክክል ነው ያሉት ኘሬዝዳንቱ ከአሚኮ ጋር በትብብር የሚዘጋጅ “የጥበብ ዐይኖች” የሚል አዲስ የቴሌቪዥን ኘሮግራም እንደሚጀመር ጠቁመው ማኅበረሰቡ እንዲከታተለው አሳስበዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከአሚኮ ጋር በትብብር በየሁለት ሳምንቱ ለተመልካች የሚደርስ የቴሌቪዥን ኘሮግራም ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
