የስጋ ደዌ በሽታ ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል።

13

 

ባሕር ዳር: የካቲት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ እና ከአማራ ክልል ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ማኅበር ጋር በመተባበር “ስጋ ደዌን አንዘንጋ” በሚል መሪ መልዕክት የፓናል ውይይት እያካሄደ ነው።

ውይይቱ በዓለም ለ72ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ27ኛ ጊዜ የእየተከበረ የሚገኘውን የስጋ ደዌ ቀን ታሳቢ ያደረገ ነው።

የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ንጹህ ሽፈራው የዓለም ጤና ድርጅት በ2018 ባወጣው መረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ210 ሺህ በላይ፤ በአፍሪካ ደግሞ 20 ሺህ ሰዎች በየ ዓመቱ በስጋ ደዌ በሽታ እንደሚጠቁ አንስተዋል።

የዓለም የስጋ ደዌ ቀን የስጋ ደዌ ተጠቂዎች የነበረባቸውን መገለል እና የሰብዓዊ መብት መገፈፍን ለዓለም ሕዝብ እና መንግሥታት ለማሳወቅ እና እርምጃ እንዲወስዱ ለማድረግ መጀመሩን ተናግረዋል።

የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎች እኩል ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ፤ በአግባቡ እንዲታከሙ እና ኅብረተሰቡ ያለውን አሉታዊ አመለካከት እንዲያስወግድ ዓለማቀፍ እና ሀገር አቀፍ ሕጎችን ማስተማወቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የስጋ ደዌ ተጠቂዎች በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ ገልጸዋል።

ቢሮው የበሽታው ተጠቂዎችን በማኅበር በማደራጀት ለመብታቸው እንዲታገሉ ማድረጉንም አንስተዋል። በክልሉ 35 የስጋ ደዌ ማኅበራት ተቋቁመው ለመብታቸው እየታገሉ መኾኑን ነው የገለጹት።

ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመቀናጀት የመከላከል፣ አድሎ እና መገለልን የማስቆም እንዲሁም በወቅቱ ሕክምና እንዲያገኙ የማስቻል ሥራ እየተገናወነ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ማኅበር ሠብሣቢ ምንይችል ደምለው ህሙማን ባለፉት ጊዜያት ባሕላዊ ሕክምናን እየመረጡ በማኅበረሰቡ ዘንድ እየተገለሉ ቀያቸውን ለቀው እንዲፈናቀሉ ኾነዋል ነው ያሉት።
አሁን ላይ በተከናወኑ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች የተሻለ ነገር መኖሩን ያነሱት ሠብሣቢው አሁን ላይ በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል የበሽታው ተጠቂዎች እየተገለሉ ይገኛሉ ብለዋል።

የስጋ ደዌ በሽታን በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ሕክምና እንዲያገኙ መሥራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምርጫ ቦርድ 48 የፖለቲካ ፖርቲዎችን የመወዳደሪያ ምልክት አስተዋወቀ።
Next articleየብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቀቀ ።