የፖለቲካ ፓርቲዎች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት እያደረጉ ነው።

14

 

ባሕር ዳር: የካቲት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመጭው ግንቦት ወር እንደሚካሄድ ይፋ መደረጉ ይታወቃል። በቅድመ ምርጫ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የፓርቲዎችን ሕጋዊ ሰውነትን ማረጋገጥ፣ አስፈላጊ መስፈርቶችን ማሟላት፣ ዕጩዎችን መመዝገብ እና ማደራጀት ይገኙበታል።

የቅድመ ምርጫ ዝግጅት በተለይም ፓርቲዎች የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን የሚያዘጋጁበት፤ ለሕዝቡ ይበጃሉ ያሏቸውን የፖሊሲ አማራጮችን በዝርዝር የሚያስቀምጡበት፣ ለሕዝቡም የሚያስተዋውቁበት ወቅት ነው።

አሚኮ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችም በምርጫው ለመሳተፍ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን ተናግረዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የኾኑት እመቤት ከበደ ፓርቲያቸው በምርጫ ታሪክ ልምድ ያለው መኾኑን ገልጸዋል። በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን ቀደም ብሎ መጀመሩንም ተናግረዋል።

የፓርቲውን አደረጃጀት እና መዋቅር በመጠቀም ለአባላት ግንዛቤ የመፍጠር እና የማንቃት ተግባር መሠራቱንም አንስተዋል።

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ባወጣው አስቻይ ቦታዎች የዕጩዎችን ምዝገባ እያካሄደ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በዚህም በርካታ ዕጩዎችን ማዘጋጀቱን ነው የጠቆሙት።

ምርጫው ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲኾንም አባላት እና ደጋፊዎቻቸው የበኩላቸውን ሚና እንዲያበረክቱ እያስገነዘበ ስለመኾኑም አመላክተዋል።

አብን መንግሥት መኾን የሚፈልገው በካርድ ብቻ መኾኑን በማመን በመራጮች ምዝገባ ወቅት መላው የፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች ካርድ እንዲያወጡ እና በንቃት እንዲሳተፉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ምክትል ሰብሳቢ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሀብቴ በላይ ፓርቲያቸው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር በምርጫው ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረገ ነው።

በጥምረት በመሠረቱት “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” በሚለው ፓርቲያቸው አማካኝነትም ማኒፌስቶ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ለማስተዋወቅ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙም ነው የተናገሩት። በምርጫው የሚሳተፉ በርካታ እጩዎችን እየመለመለ እንደሚገኝም አንስተዋል።

አባላትን እና ደጋፊዎቻቸውን እንደልብ ለማግኘት እና ሕዝባዊ ውይይቶችን ለማካሄድ በመንግሥት እና በምርጫ ቦርድ በኩል አስቻይ ሁኔታ ሊመቻች እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ተወካይ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር ፓርቲያቸው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ፓርቲው ሀገር ዓቀፍ ፓርቲ መኾኑን ጠቅሰው አስቻይ በኾነባቸው ቦታዎች ሁሉ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለመወዳደር የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል።

አባላት እና ደጋፊዎቻቸውን ማንቃት እና ግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም እጩዎችን የመመልመል ተግባራትን እያከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየገራይን ሐይቅ ለማዳን ምን እየተሠራ ነው?