የገራይን ሐይቅ ለማዳን ምን እየተሠራ ነው?

9

 

ፍኖተ ሰላም: የካቲት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከምዕራብ ጎጃም ዞን ርእሰ መዲና ፍኖተ ሰላም ከተማ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው አስፋልት መንገድ ላይ 2 ኪሎ ሜትር ያህል እንደተጓዝን ከመንገዱ ወደ ደቡብ አቅጣጫ 500 ሜትር ርቀት አካባቢ ላይ የገራይ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ይገኛል።

ሐይቁ በ1971 ዓ.ም ለመስኖ ሥራ አገልግሎት የተሠራ ነው፡፡ የሐይቁ ጥልቀት 6 ሜትር አካባቢ እንደሚኾን ይነገራል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች በዓሳ ማስገር እና በመስኖ ልማት በስፋት ተሠማርተውበት የሚገኝ ሐይቅ ነው።

ወጣት መላኩ አየናቸው የገራይ ሐይቅ አካባቢ ነዋሪ ነው። ለበርካታ ዓመታት በግል እና በማኅበር በመደራጀት በዓሳ ማስገር ሥራ ተሠማርተዋል። ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አምባ ጉዞ ለፍሬ ኅብረት ሥራ ማኅበር ውስጥ በመደራጀት ዓሳ በማስገር ሥራ መቆየታቸውን ገልጿል። በዚህም ለፍኖተ ሰላም ከተማ ዓሳ በማቅረብ የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበር አጫውቶናል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ሕገ ወጥ አስጋሪዎች በመኖራቸው ለሥራቸው እንቅፋት ፈጥሮባቸዋል።

በተጨማሪም የሐይቁ ደኅንነት በተገቢው መንገድ ባለመጠበቁ የዓሳ ሀብቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱንም ተናግሯል። የተቋቋመው ማኅበር በመፍረሱም በግሉ በዓሳ ማስገር ሥራ ሕይወቱን እየገፋ እንደሚገኝ ነው የተናገረው።

ሌላው የአካባቢው አርሶ አደር ይነበብ አምዴ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከሐይቁ በሚያገኘው ውኃ በመስኖ ልማት ተሠማርቷል። በዚህም እሱን ጨምሮ በርካታ አርሶ አደሮች በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጿል። ከዚህ በፊት የሐይቁ ውኃ ከግድቡ ኮርቻ በማለፍ በቂ ውኃ እንደሚለቅ እና የመስኖ ሥራቸውን ሲያሳልጥላቸው መቆየቱን አውስቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የውኃ መጠኑ እየቀነሰ መምጣቱን ነግሮናል። ውኃው ከነበረበት ቦታ ወደ ኋላ እየቀነሰ መምጣቱንም አስረድቷል። በተጨማሪም ሐይቁ በተለምዶ ”አለምሲሳ” በተሰኘ አረም በከፍተኛ ሁኔታ መወረሩን አርሶ አደሩ ተናግሯል።

በሐይቁ ላይ ከዚህ የከፋ ችግር ሳይደርስ ሁሉም ርብርብ በማድረግ እንዲታደገው አርሶ አደሮች ጠይቀዋል።

የጃቢጠህናን ወረዳ አካባቢ እና ደን ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዳኛቸው ታደሰ የገራይ ሰው ሠራሽ ሐይቅ በአካባቢው ለሚገኙ ከ5 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በመስኖ ልማት ተጠቃሚ እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

የሰው ሠራሽ ሐይቁ ዙሪያ ገባ የፈጠረው ሥነ ምኅዳር የተለያዩ እፅዋት እና እንስሳት መገኛ ጭምርም እንደኾነ ነው የተናገሩት። አካባቢው ለቱሪስት ምቹ እና ከፍተኛ ተዝናኖት የሚፈጥር በመኾኑ ለቱሪዝም ዘርፉም አቅም ያለው ሐይቅ መኾኑን ኀላፊው ተናግረዋል። ይሁን እንጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሐይቁ ችግር እንደተጋረጠበት አረጋግጠዋል።

በየጊዜው ከአካባቢው ወደ ሐይቁ በሚመጣ የጎርፍ ደለል በመሞላቱ እና ውኃው እየሰረገ በመኾኑ የውኃ መጠኑ እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል። በሐይቁ ዙሪያ ያሉ የዱር እንስሳት እና እፅዋትም የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ጠቁመዋል።

የሐይቁን ደኅንነት በሚፈለገው ልክ ለማስጠበቅ የጸጥታ ችግሩ ከፍተኛ ተግዳሮት መፍጠሩንም ኀላፊው ተናግረዋል። ቀጣይ የሐይቁን ደኅንነት ለማስጠበቅ ኮሚቴ በማቋቋም በዘላቂነት ለመፍታት ከአጋር አካላት ጋር በመኾን ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ከእንስሳት ንክኪ እና ለሐይቁ ስጋት ከኾኑ ነገሮች በመታቀብ የበኩሉንም እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ ንጉስ ስንታየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የምሥረታ ክብረ በዓል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በወንዶ ገነት እየተከበረ ነው።
Next articleየፖለቲካ ፓርቲዎች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት እያደረጉ ነው።