ሴቶች በቂ የውክልና ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል።

5
ደሴ: የካቲት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “በሴቶች ተሳትፎ የጸናች እና የበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልዕክት የደቡብ ወሎ ዞን ሴት የመንግሥት ሠራተኞች ምክክር አካሂደዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ ሴት የመንግሥት ሠራተኞች በሀገራችን የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ማደግ እንደሚገባው አንስተዋል። የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ከሚጠናከርባቸው መንገዶች አንዱ በምርጫ መሳተፍ በመኾኑ በመጭው ሀገራዊ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።
መድረኩ ለሴቶች ግንዛቤ በመፍጠር በምርጫው በመራጭነት፣ በአሥፈጻሚነት በንቃት እንዲሳተፉ፤ ለሌሎችም ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ዝግጅት የተደረገ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞን ሴቶች ክንፍ ኀላፊ የሺሐረግ ሰይድ ናቸው።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ኀላፊ ኢሌኒ ዓባይ በሀገራችን የምርጫ ታሪክ የሴቶች ተሳትፎ እየተሻሻለ ስለመምጣቱ ነው የተናገሩት።
በተለይም መንግሥት ለሴቶች ተሳትፎ የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ እንደኾነም ገልጸዋል። በቀጣዩ ምርጫ 40 ከመቶ እጩዎች ሴቶች እንደሚኾኑም ጠቁመዋል።
የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር የቋንቋ ልማት ሚኒስትር ዲኤታ ነፊሳ አልማሀዲ የብልጽግና ፓርቲ እንደ ፓርቲም ኾነ እንደ መንግሥት ለሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ከፍተኛ ትኩረት በመሰጠቱ በከፍተኛ የመሪነት ቦታዎች ላይ ሴቶች መሳተፍ እንደቻሉ ጠቁመዋል።
“ሴቶች የማኅበረሰቡ ግማሽ እንደመኾናቸው በቂ የውክልና ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚገባ የተናገሩት ሚኒስትር ዲኤታዋ በፖለቲካው መስክ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል” ብለዋል።
ዘጋቢ:- ከድር አሊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁስ እሸጋ እና ስርጭት መጀመሩ ተገለጸ።
Next article“የራስ ታሪክን እና ሃብት በእሳት ማውደም ኢትዮጵያዊ ነኝ ከሚል አካል አይጠበቅም” የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዎች