
ደብረ ታቦር፡ የካቲት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር የጥፋት ኀይሎች ከሰሞኑ በከተማዋ በመሠረተ ልማቶች ላይ ያደረሱትን ጥፋት አስመልክቶ ውይይት አድርጓል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ሰላምን ለማምጣት የመንግሥት ሠራተኛው ሚና ወሳኝ መኾኑን ጠቁመዋል ለዚህም ይረዳ ዘንድ ሕዝቡን በማሳተፍ ሰፊ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን መሥራት፣ የጸጥታ መዋቅሩን በሥነ-ልቦና ማንቃት እና በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዋ የመንግሥት ሠራተኛ ሃሳብ ሰጭ የሰላም እጦቱ በአካባቢው ላይ ያሳደረው ጫና ከባድ መኾኑን አንስተዋል።
በድህነት ላይ ለበለጠ ድህነት እየዳረጋቸው መኾኑንም ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ ስለሰላም መዘከር እና መምከር እንዳለበትም በውይይቱ በስፋት ስለመነሳቱ ነው የጠቆሙት።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከዚህ በፊት ተፈጥሮ እና ተከስቶ የማያውቅ ነው ብለዋል። ያልተጠበቀ ድርጊት ከመፈጸሙ ባለፈ ኅበረተሰቡን ለእንግልት እንደዳረገውም ጠቁመዋል።
በውይይቱ ላይ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት መግባባት ላይ መደረሱንም አንስተዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ትልቁን ድርሻ ወስደው ድርጊቱን ማውገዝ እና በቃቹህ ማለት አለባቸውም ብለዋል።
በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ የዞኑ አሁናዊ ሁኔታ የሰላም ስኬት የሚረጋገጠው በጽናት በመቆም እንደኾነም አስረድተዋል።
ከታሪካዊ ጠላት ጋር ያልተገባ ጋብቻ ፈጽመው ሀገር ለማውደም የተነሱትን ኀይሎች ሕዝቡ በውል የተረዳበት ወቅት መኾኑንም አንስተዋል።
መንግሥት ቀጣይ በአጥፊ ኀይሎች ላይ ከማኅበረሰቡ ጋር በጋራ በመኾን ሕግ የማስከበር ሥራ እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
