
ገንዳ ውኃ፡ የካቲት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳዳር ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ወጣቶች በመጭው ግንቦት ወር የሚካሄደው 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ ነፃ እና ዴሞክራሲዊ ኾኖ እንዲካሄድ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በምርጫው ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ወጣቶቹ ምርጫ ዜጎች አካባቢያቸውን የሚያለማላቸውን እና የሥራ ዕድል የሚፈጥርላቸውን መንግሥት ለመምረጥ የሚያስችላቸው መንገድ መኾኑን አንስተዋል።
ምርጫው ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲካሄድ የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ የበኩላቸውን ኀላፊነት እንደሚወጡም አስታውቀዋል።
መንግሥት የሚቀየረው በአመጽ፣ በጦርነት እና እርስ በእርስ በመጋጨት ሳይኾን በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመኾኑ ወጣቶች ይህን በመረዳት በምርጫው መሳተፍ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላምን የሚያሰፍን፣ ልማትን የሚያፋጥን፣ መሠረተ ልማቶችን የሚያሟላ፣ ለዜጎች ሰብዓዊነት መብት የሚቆረቆር እና ዴሞክራሲን የሚገነባ መንግሥት እንደሚፈልጉም ወጣቶቹ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
