
ደብረማርቆስ፡ የካቲት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች በከተማዋ በማምረት ላይ ያሉ እና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ወጣቶቹ በጉብኝታቸው ወቅት እንደተናገሩት ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት መግባታቸው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እና የሀገርን ኢኮኖሚ ከፍ ለማድረግ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ ነው።
እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸው ባለፈ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እና የአካባቢውን ጥሬ ዕቃ በግብዓትነት ለመጠቀም ያላቸው ፋይዳ ከፍ ያለ መኾኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በግንባታ ላይ የሚገኙ ተጨማሪ ኢንዱስትሪዎችም ለወደፊት ተስፋ ሰጭ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ተመሥገን ተድላ የሚገነቡ ፋብሪካዎች ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መኾኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ1ሺህ 200 በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪዎቹ ተኪ ምርቶችን በማምረት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ወጭ እንደሚያስቀሩም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማ አሥተዳደሩ ከ240 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ 94 የሚኾኑት ወደ ምርት በመግባት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
